2Kings (14/25)  

1. በእስራኤል ንጉሥ በኢዮአካዝ ልጅ በዮአስ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ።
2. መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
3. በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ኢዮአስ እንዳደረገ ሁሉ እንጂ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም።
4. ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉት መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶች ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር።
5. መንግሥቱም በጸናለት ጊዜ አባቱን የገደሉትን ባሪያዎች ገደለ።
6. በሙሴ ሕግ መጽሐፍም እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔርም። ሁሉ በኃጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆች አይሙቱ፥ ልጆችም በአባቶች አይሙቱ ብሎ እንዳዘዘ የነፍሰ ገዳዮቹን ልጆች አልገደለም።
7. እርሱም በጨው ሸለቆ ከኤዶምያስ አሥር ሺህ ሰው ገደለ፤ ሴላን በሰልፍ ወስዶ ስምዋን እስከ ዛሬ ድረስ ዮቅትኤል ብሎ ጠራት።
8. በዚያን ጊዜም አሜስያስ። ና እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞችን ላከ።
9. የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ። የሊባኖስ ኵርንችት፥ ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው ብሎ ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኵርንችቱን ረገጠ።
10. ኤዶምያስን በእውነት መታህ፥ ልብህንም ከፍ ከፍ አደረግህ፤ በዚያ ተመካ፥ በቤትህም ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር ትወድቅ ዘንድ ስለ ምን መከራ ትሻለህ? ብሎ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ላከ።
11. አሜስያስ ግን አልሰማም፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወጣ፥ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤት ሳሚስ እርስ በርሳቸው ተያዩ።
12. ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ።
13. የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስክ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ።
14. ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሡ ቤት መዛግብት የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ በመያዣም የተያዙትን ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
15. የቀረውም ያደረገው የዮአስ ነገር፥ ጭከናውም፥ ከይሁዳም ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንደ ተዋጋ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
16. ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮርብዓም በፋንታው ነገሠ።
17. የይሁዳም ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከዮአስ ሞት በኋላ አሥራ አምስት ዓመት ኖረ።
18. የቀረውም የአሜስያስ ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
19. በኢየሩሳሌምም የዓመፅ መሐላ አደረጉበት፥ እርሱም ወደ ለኪሶ ኰበለለ፤ በኋላውም ወደ ለኪሶ ላኩ፥ በዚያም ገደሉት።
20. በፈረስም ጭነው አመጡት፥ በኢየሩሳሌምም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ።
21. የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ የነበረውን ዓዛርያስን ወስዶ በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሠው። 20፤ ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ፥ ኤላትን ሠርቶ ወደ ይሁዳ መለሳት። 23፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ልጅ በአሜስያስ በአሥራ አምስተኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ አርባ አንድ ዓመትም ነገሠ። 24፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ እስራኤልንም ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት ሁሉ አልራቀም። 25፤ የጋትሔፌር በነበረው በአማቴ ልጅ በባሪያው በነቢዩ በዮናስ እጅ እንደ ተናገረው እንደ እስራኤል አምላክ እንደ እግዚአብሔር ቃል የእስራኤልን ድንበር ከሐማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ መለሰ። 26፤ የታሰረውና የተለቀቀውም እንደ ጠፋ፥ እስራኤልንም የሚረዳ እንዳልነበረ እግዚአብሔር እጅግ የመረረውን የእስራኤልን ጭንቀት አየ። 27፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ስም ከሰማይ በታች ይደመስስ ዘንድ አልተናገረም፤ ነገር ግን በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም እጅ አዳናቸው። 28፤ የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ እንደ ተዋጋም፥ የይሁዳ የነበረውን ደማስቆንና ሐማትን ለእስራኤል እንደ መለሰ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 29፤ ኢዮርብዓምም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዘካርያ በፋንታው ነገሠ።

  2Kings (14/25)