2Kings (13/25)  

1. በይሁዳ ንጉሥ በአካዝያስ ልጅ በኢዮአስ በሀያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ አሥራ ሰባትም ዓመት ነገሠ።
2. በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፥ እስራኤልንም ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኃጢአት ተከተለ፤ ከእርስዋም አልራቀም።
3. የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በዘመኑም ሁሉ በሶርያው ንጉሥ በአዛሄል እጅ፥ በአዛሄልም ልጅ በወልደ አዴር እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር።
4. ኢዮአካዝም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ያስጨነቀበትን ጭንቀት አይቶአልና ሰማው።
5. እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታዳጊ ሰጠ፥ ከሶርያውያንም እጅ ዳኑ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ቀድሞው ጊዜ በድንኳናቸው ተቀመጡ።
6. ነገር ግን በእርስዋ ሄዱ እንጂ እስራኤልን ካሳተው ከኢዮርብዓም ቤት ኃጢአት አልራቁም፤ ደግሞም የማምለኪያ ዐፀድ በሰማርያ ቆሞ ቀረ።
7. ለኢዮአካዝም ከአምሳ ፈረሰኞች፥ ከአሥርም ሰረገሎች፥ ከአሥር ሺህም እግረኞች በቀር ሕዝብ አልቀረለትም፤ የሶርያ ንጉሥ አጥፍቶአቸዋልና፥ በአውድማም እንዳላ ዕብቅ አድቅቆአቸዋልና።
8. የቀረውም የኢዮአካዝ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
9. ኢዮአካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት፤ ልጁም ዮአስ በፋንታው ነገሠ።
10. በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ አሥራ ስድስትም ዓመት ነገሠ።
11. በእግዚአብሔር ፊት ክፋ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን በሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት ሁሉ ሄደ እንጂ ከእርስዋ አልራቀም።
12. የቀረውም የዮአስ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከይሁዳም ከአሜስያስ ጋር የተዋጋበት ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
13. ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ ኢዮርብዓምም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ።
14. ኤልሳዕም በሚሞትበት በሽታ ታመመ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ ወርዶ በፊቱ አለቀሰና። አባቴ ሆይ፥ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች አለ።
15. ኤልሳዕም። ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ አለው፤ ቀስቱንና ፍላጻዎችንም ወሰደ።
16. የእስራኤልንም ንጉሥ። እጅህን በቀስቱ ላይ ጫን አለው። እጁንም ጫነበት፤ ኤልሳዕም እጁን በንጉሡ እጅ ላይ ጭኖ።
17. የምስራቁን መስኮት ክፈት አለ፤ ከፈተውም። ኤልሳዕም። ወርውር አለ፤ ወረወረውም። እርሱም። የእግዚአብሔር መድኃኒት ፍላጻ ነው፤ በሶርያ ላይ የመድኃኒት ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ሶርያዊያንን በአፌቅ ትመታለህ አለ።
18. ደግሞም። ፍላጻዎቹን ውሰድ አለው፤ ወሰዳቸውም። የእስራኤልንም ንጉሥ። ምድሩን ምታው አለው። ሦስት ጊዜም መትቶ ቆመ።
19. የእግዚአብሔርም ሰው ተቆጥቶ። አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ኖሮ ሶርያን እስክታጠፋው ድረስ በመታኸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ አለ።
20. ኤልሳዕም ሞተ፥ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር።
21. ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፥ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዮው ድኖ በእግሩ ቆመ።
22. የሶርያም ንጉሥ አዛሄል በኢዮአካዝ ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስጨነቀ፤
23. እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፥ ማራቸውም፥ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ስላደረገውም ቃል ኪዳን እነርሱን ተመለከተ፤ ሊያጠፋቸውም አልወደደም፥ ፈጽሞም ከፊቱ አልጣላቸውም።
24. የሶርያም ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁም ወልደ አዴር በፋንታው ነገሠ።
25. አዛሄልም ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በሰልፍ የወሰዳቸውን ከተሞች የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከአዛሄል ልጅ ከወልደ አዴር እጅ ወሰደ። ዮአስም ሦስት ጊዜ መታው፥ የእስራኤልንም ከተሞች መለሰ።

  2Kings (13/25)