← 2Corinthians (6/13) → |
1. | አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ |
2. | በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው። |
3. | አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። |
4. | ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ |
5. | በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ |
6. | በመጦም፥ በንጽህና፥ በእውቀት፥ በትዕግሥት፥ በቸርነት፥ በመንፈስ ቅዱስ፥ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፥ በእውነት ቃል፥ |
7. | በእግዚአብሔር ኃይል፥ ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፥ በክብርና በውርደት፥ |
8. | በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፤ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ |
9. | ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ |
10. | ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። |
11. | እናንተ የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፥ አፋችን ለእናንተ ተከፍቶአል ልባችንም ሰፍቶላችኋል፤ |
12. | በእኛ አልጠበባችሁም በሆዳችሁ ግን ጠቦባችኋል፤ |
13. | ልጆቼ እንደ መሆናችሁ ግን እላችኋለሁ፥ እናንተ ደግሞ ብድራት መልሳችሁልን ተስፋፉ። |
14. | ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? |
15. | ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? |
16. | ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል። በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። 17-18 ስለዚህም ጌታ። ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ። እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል። |
← 2Corinthians (6/13) → |