← 2Corinthians (4/13) → |
1. | ስለዚህ ምክንያት ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም። |
2. | ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን። |
3. | ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። |
4. | ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ። |
5. | ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥ ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን። |
6. | በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ። በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና። |
7. | ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ |
8. | በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ |
9. | እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ |
10. | የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። |
11. | የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና። |
12. | ስለዚህ ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል። |
13. | ነገር ግን። አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን፤ |
14. | ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛን ደግሞ ከኢየሱስ ጋር እንዲያስነሣን ከእናንተም ጋር እንዲያቀርበን እናውቃለንና። |
15. | በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና። |
16. | ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 17-18 የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። |
← 2Corinthians (4/13) → |