| ← 2Chronicles (4/36) → |
| 1. | ደግሞም ርዝመቱ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም አሥር ክንድ የነበረውን የናሱን መሠዊያ ሠራ። |
| 2. | ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር አሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ። |
| 3. | በበታቹም ለአንድ ክንድ አሥር፥ ለአንድም ክንድ አሥር፥ ጕብጕቦች አዞረበት፤ ኵሬውም በቀለጠ ጊዜ ጕብጕቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር። |
| 4. | በአሥራ ሁለትም በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን ሦስቱም ወደ ምዕራብ ሦስቱም ወደ ደቡብ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር፤ ኵሬውም በላያቸው ነበር፥ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ። |
| 5. | ውፍረቱም አንድ ጋት ያህል ነበረ፤ ከንፈሩም አንደ ጽዋ ከንፈር፥ እንደ ሱፍ አበባ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ሦስት ሺህም የባዶስ መሥፈሪያ ይይዝ ነበር። |
| 6. | ደግሞም አሥር የመታጠቢያ ሰኖች ሠራ፥ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበው ነገር ሁሉ ይታጠብባቸው ዘንድ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ አኖራቸው፤ ኵሬው ግን ካህናት ይታጠቡበት ነበር። |
| 7. | አሥሩንም መቅረዞች እንደ ሥርዓታቸው ከወርቅ ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። |
| 8. | አሥሩንም ገበታዎች ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። አንድ መቶም የወርቅ ድስቶች ሠራ። |
| 9. | ደግሞም የካህናቱን አደባባይ፥ ታላቁንም አደባባይ፥ የአደባባዩንም ደጆች ሠራ፥ ደጆቻቸውንም በናስ ለበጠ። |
| 10. | ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው። |
| 11. | ኪራምም ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹን ድስቶቹንም ሠራ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ። |
| 12. | ሁለቱን አዕማድ፥ ጽዋዎቹንም፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለት ጕልላቶች፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን የጕልላቶች ሁለቱን ጽዋዎች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች ሠራ። |
| 13. | በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ፥ ለእያንዳንዱ መርበብ ሁለት ሁለት ተራ ሮማኖች፥ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ። |
| 14. | መቀመጫዎቹንና በመቀመጫዎቹ ላይ የሚቀመጡትን የመታጠቢያ ሰኖች፥ |
| 15. | አንዱንም ኵሬ፥ በበታቹም የሚሆኑትን አሥራ ሁለት በሬዎች ሠራ። |
| 16. | ምንቸቶቹንም መጫሪያዎቹንም ሜንጦዎቹንም ዕቃቸውንም ሁሉ ኪራም ለንጉሡ ለሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት ከለስላሳ ናስ ሠራ። |
| 17. | ንጉሡም በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጽሬዳ መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው። |
| 18. | ሰሎሞንም እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ እጅግ አብዝቶ ሠራ፤ የናሱም ሚዛን አይቈጠርም ነበር። |
| 19. | ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ የወርቁንም መሠዊያ፥ የገጹንም ኅብስት የነበረባቸውን ገበታዎች፥ |
| 20. | በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት እንደ ሥርዓታቸው ያበሩ ዘንድ መቅረዞችንና ቀንዲሎቻቸውን ከጥሩ ወርቅ ሠራ። |
| 21. | አበባዎቹንና ቀንዲሎቹን መኮስተሪያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። |
| 22. | ጕጦቹንም ድስቶቹንም ጭልፋዎቹንም ማንደጃዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። የውስጠኛውም ቤት የቅድስተ ቅዱሳን ደጆች የቤተ መቅደሱም ደጆች የወርቅ ነበሩ። |
| ← 2Chronicles (4/36) → |