2Chronicles (31/36)  

1. ይህም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ በዚያ የተገኙ እስራኤል ሁሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው ሁሉን ፈጽመው እስካጠፉአቸው ድረስ ሐውልቶቹን ሰባበሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጡ፥ በይሁዳና በብንያምም ሁሉ ደግሞም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኮረብታው መስገጃዎችና መሠዊያዎች አፈረሱ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ርስታቸውና ወደ ከተሞቻቸው ተመለሱ።
2. ሕዝቅያስም የካህናትንና የሌዋውያንን ሰሞን በየክፍላቸውና በየአገልግሎታቸው አቆመ፤ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ በሮች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ያገለግሉም ዘንድ፥ ያመሰግኑም ያከብሩም ዘንድ ካህናቱንና ሌዋውያኑን አቆመ።
3. በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ተጻፈ በጥዋትና በማታ፥ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በበዓላትም ለሚቀርበው ለሚቃጠለው መሥዋዕት ንጉሡ ከገንዘቡ የሚከፍለውን ወሰነ።
4. በእግዚአብሔርም ቤት ለአገልግሎት እንዲጸኑ ለካህናቱና ለሌዋውያን ክፍላቸውን ይሰጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ አዘዘ።
5. ይህንም ነገር እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች የእህሉንና የወይኑን ጠጅ የዘይቱንና የማሩንም፥ የእርሻውንም ፍሬ ሁሉ በኵራት ሰጡ፤ የሁሉንም አሥራት አብዝተው አቀረቡ።
6. በይሁዳም ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳ ልጆች የበሬውንና የበጉን አሥራት፥ ለአምላካቸውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን አሥራት አመጡ፥ ከምረውም አኖሩት።
7. በሦስተኛው ወር መከመር ጀመሩ፤ በሰባተኛውም ወር ጨረሱ።
8. ሕዝቅያስና አለቆቹም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርና ሕዝቡን እስራኤልን ባረኩ።
9. ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቀ።
10. ከሳዶቅም ወገን የሆነ ዋነኛው ካህን ዓዛሪያስ። ሕዝቡ ቍርባኑን ወደ እግዚአብሔር ቤት ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ በልተናል፥ ጠግበናልም፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ባርኮአልና ብዙ ተርፎአል፤ የተረፈውም ይህ ክምር ትልቅ ነው ብሎ ተናገረ።
11. ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤት ጐተራ ያዘጋጁ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም አዘጋጁ።
12. ቍርባኑና አሥራቱን የተቀደሱትንም በእምነት ወደዚያ አገቡት። ሌዋዊውም ኮናንያ ተሾመባቸው፥ ወንድሙም ሰሜኢ በማዕርግ ሁለተኛ ነበረ፤
13. በንጉሡም በሕዝቅያስና በእግዚአብሔር ቤት አለቃ በዓዛርያስ ትእዛዝ ይሒዒል፥ ዓዛዝያ፥ ናሖት፥ አሣሄል፥ ይሬሞት፥ ዮዛባት፥ ኤሊኤል፥ ሰማኪያ፥ መሐት፥ በናያስ፥ ከኮናንያና ከወንድሙ ከሰሜኢ እጅ በታች ተቈጣጣሪዎች ነበሩ።
14. የሌዋዊውም የይምና ልጅ የምሥራቁ ደጅ በረኛ ቆሬ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትን ነገሮች እንዲያካፍል ሕዝቡ ለእግዚአብሔር በፈቃድ ባቀረቡት ላይ ተሾመ።
15. በካህናቱም ከተሞች ለታላላቆችና ለታናናሾች ወንድሞቻቸው በየሰሞናቸው ክፍላቸውን በእምነት ይሰጡ ዘንድ ዔድን፥ ሚንያሚን፥ ኢያሱ፥ ሸማያ፥ አማርያ፥ ሴኬንያ ከእጁ በታች ነበሩ።
16. ከሦስትም ዓመት ወደ ላይ ላሉ በየሰሞናቸው ለሥራቸውና ለአገልግሎታቸው ዕለት ዕለት ወደ እግዚአብሔር ቤት ለሚገቡ ወንዶች ሁሉ፤
17. በየአባቶቻቸውም ቤት ለተቈጠሩ ካህናት፥ ከሀያ ዓመትም ወደ ላይ ላሉ በየሥርዓታቸውና በየሰሞናቸው ለተቈጠሩ ሌዋውያን፥
18. በማኅበሩም ሁሉ በየትውልዳቸው ለተቈጠሩ ለሕፃናቶቻቸውና ለሚስቶቻቸው ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻቸውም ይሰጡ ነበር፤ በእምነት ተቀድሰዋልና።
19. በየከተማይቱም ሁሉ በከተማቸው መሰምርያዎቹ ላሉ ለአሮን ልጆች ለካህናቱ፥ ከካህናቱም ወገን ላሉ ወንዶች ሁሉ፥ በትውልዳቸውም ለተቈጠሩ ሌዋውያን ሁሉ ክፍላቸውን ይሰጡ ዘንድ በስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ።
20. ሕዝቅያስም በይሁዳ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት መልካምንና ቅንን ነገር እውነትንም አደረገ።
21. ስለ እግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት በጀመረው ሥራ ሁሉ፥ በሕጉና በትእዛዙም፥ አምላኩን ለመፈለግ በፍጹም ልቡ አደረገው፥ ተከናወነለትም። ቸ

  2Chronicles (31/36)