2Chronicles (29/36)  

1. ሕዝቅያስም የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ በነበረ ጊዜ መንገሥ ጀመረ፥ በኢየሩሳሌም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ትባል ነበር።
2. አባቱም ዳዊት እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
3. በነገሠም በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤት ደጆች ከፈተ፥ አደሳቸውም።
4. ካህናቱንና ሌዋውያኑንም አስመጣ፥ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይም ሰበሰባቸው፥
5. እንዲህም አላቸው። ሌዋውያን ሆይ፥ ስሙኝ፤ ተቀደሱ፥ የአባቶቻችሁንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ቀድሱ፤ ርኩሱን ነገር ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ።
6. አባቶቻችን ተላልፈዋል፥ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ትተዋል፥ ፊታቸውንም ከእግዚአብሔር መኖሪያ መልሰዋል፥
7. ወደ እርስዋም ጀርባቸውን አዙረዋል፤ ደግሞም የወለሉን ደጆች ቈልፈዋል፥ መብራቶቹንም አጥፍተዋል፥ በመቅደሱም ውስጥ ለእስራኤል አምላክ አላጠኑም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አላቀረቡም።
8. ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ሆነ፥ በዓይናችሁም እንደምታዩ ለድንጋጤና ለመደነቂያ ለመዘበቻም አሳልፎ ሰጣቸው።
9. እነሆም፥ ስለዚህ አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ሚስቶቻችንም ተማረኩ።
10. አሁንም የቍጣው ጽናት ከእኛ እንዲመለስ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን አደርግ ዘንድ በልቤ አስቤአለሁ።
11. ልጆቼ ሆይ፥ በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ።
12. ሌዋውያኑም፥ ከቀዓት ልጆች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፥ ከሜራሪም ልጆች የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፥ ከጌድሶንም ልጆች የዛማት ልጅ ዩአክና የዩአክ ልጅ ዔድን፥
14. ከኤሊጸፋንም ልጆች ሺምሪና ይዒኤል፥ ከአሳፍም ልጆች ዘካርያስና መታንያ፥ ከኤማንም ልጆች ይሒኤልና ሰሜኢ፥ ከኤዶታምም ልጆች ሸማያና ዑዝኤል ተነሡ።
15. ወንድሞቻቸውንም ሰብስበው ተቀደሱ፤ በእግዚአብሔር ቃል እንደመጣው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ የእግዚአብሔርን ቤት ያነጹ ዘንድ ገቡ።
16. ካህናቱም ያነጹት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጡ ገቡ፥ በእግዚአብሔርም መቅደስ ያገኙትን ርኩስ ነገር ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ቤት አደባባይ አወጡት። ሌዋውያንም ወስደው ወደ ሜዳ ወደ ቄድሮን ወንዝ ጣሉት።
17. በመጀመሪያውም ወር በመጀመሪያው ቀን ይቀደሱ ጀመር፥ በዚያውም ወር በስምንተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ወለል ደረሱ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት በስምንት ቀን ቀደሱ፥ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ ስድስተኛው ቀን ፈጸሙ።
18. ወደ ውስጡም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው። የእግዚአብሔርን ቤት ሁሉ፥ ለሚቃጠል መስዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት ገበታና ዕቃውን ሁሉ አንጽተናል፤
19. ንጉሡም አካዝ ነግሦ ሳለ በመተላለፍ ያረከሰውን ዕቃ ሁሉ አዘጋጅተናል ቀድሰናልም፤ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ሆነዋል አሉት።
20. ንጉሡም ሕዝቅያስ ማልዶ ተነሣ የከተማይቱንም አለቆች ሰበሰበ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ወጣ።
21. ስለ መንግሥቱና ስለ መቅደሱም ስለ ይሁዳም ሰባት ወይፈኖች፥ ሰባትም አውራ በጎች፥ ሰባትም የበግ ጠቦቶች፥ ሰባትም አውራ ፍየሎች ለኃጢያት መሥዋዕት አመጡ። የአሮንንም ልጆች ካህናቱን። በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አሳረጉአቸው አላቸው።
22. ወይፈኖቹንም አረዱ፥ ካህናቱም ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም አረዱ፥ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ ጠቦቶቹንም አረዱ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት።
23. የኃጢያትም መሥዋዕት የሚሆኑትን አውራ ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፥ እጃቸውንም ጫኑባቸው፥ ካህናቱም አረዱአቸው፤
24. ንጉሡም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኃጢያት መሥዋዕት ለእስራኤል ሁሉ እንዲደረግ አዝዞ ነበርና ለእስራኤል ሁሉ ማስተስረያ ያደርጉ ዘንድ የኃጢያቱን መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ላይ አቀረቡ።
25. ይህንም ትእዛዝ እግዚአብሔር በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ፥ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ቤት አቆመ።
26. ሌዋውያንም የዳዊትን የዜማ ዕቃ ይዘው፥ ካህናቱም መለከቱን ይዘው ቆመው ነበር።
27. ሕዝቅያስም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ያሳርጉ ዘንድ አዘዘ፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ማረግ በተጀመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መዝሙር ደግሞ ተጀመረ፥ መለከቱም ተነፋ፥ የእስራኤልም ንጉሥ የዳዊት ዜማ ዕቃ ተመታ።
28. ጉባኤውም ሁሉ ሰገዱ፥ መዘምራኑም ዘመሩ፥ መለከተኞችም ነፉ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪፈጸም ድረስ ይህ ሁሉ ሆነ።
29. ማቅረቡንም በፈጸሙ ጊዜ ንጉሡና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ አጐነበሱ ሰገዱም።
30. ንጉሡም ሕዝቅያስና አለቆቹ ሌዋውያንን በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ አዘዙ። በደስታም አመሰገኑ፥ አጐነበሱም ሰገዱም።
31. ሕዝቅያስም። አሁን ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፤ ቅረቡ፥ መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ ብሎ ተናገረ። ጉባኤውም መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መስዋዕት አመጡ፤ ልባቸውም የፈቀደ ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አመጡ።
32. ጉባኤውም ያመጡት የሚቃጠል መሥዋዕት ቍጥር ሰባ ወይፈን፥ መቶም አውራ በጎች፥ ሁለት መቶም የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ ይህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ።
33. የተቀደሱትም ቍጥር ስድስት መቶ በሬዎች ሦስት ሺህም በጎች ነበረ።
34. ነገር ግን ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለመግፈፍ ጥቂቶች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን በቅን ልብ ከካህናት ይልቅ ይቀደሱ ነበርና ሥራው እስኪፈጸም ድረስ፥ ካህናቱም እስኪቀደሱ ድረስ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን ያግዙአቸው ነበር።
35. የሚቃጠለውም መሥዋዕት የደኅንነቱም መሥዋዕት ስብ፥ ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ሁሉ ጋር የሚቀርበው የመጠጥ ቍርባን፥ ብዙ ነበረ። እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ተዘጋጀ።
36. ሕዝቅያስና ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላዘጋጀው ነገር ደስ አላቸው። ይህም ነገር በድንገት ተደረገ።

  2Chronicles (29/36)