2Chronicles (27/36)  

1. ኢዮአታምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሳዶቅ ልጅ ኢየሩሳ ትባል ነበር።
2. አባቱም ዖዝያን እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር መቅደስ አልገባም፤ ሕዝቡም ገና ይበድል ነበር።
3. የእግዚአብሔርን ቤት የላይኛውን በር ሠራ፥ በዖፌልም ቅጥር ላይ እጅግ ሠራ።
4. በተራራማውም በይሁዳ አገር ላይ ከተሞችን ሠራ፥ በዱር ስፍራዎችም አምባዎችንና ግንቦችን ሠራ።
5. ከአሞንም ልጆች ንጉሥ ጋር ተዋጋ አሸነፋቸውም። በዚያም ዓመት የአሞን ልጆች መቶ መክሊት ብር፥ አሥር ሺህም የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ አሥር ሺህም የቆሬስ መሥፈሪያ ገብስ ሰጡት። እንዲሁም ደግሞ የአሞን ልጆች በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ሰጡት።
6. ኢዮአታምም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መንገዱን አቅንቶአልና በረታ።
7. የቀረውም የኢዮአታም ነገር፥ ሰልፉም ሁሉ፥ ሥራውም፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።
8. መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ።
9. ኢዮአታምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አካዝ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።

  2Chronicles (27/36)