2Chronicles (22/36)  

1. በኢየሩሳሌም የነበሩትም ታናሹን ልጁን አካዝያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡት። የመጣባቸው የዓረብና የአሊማዞን የሽፍቶች ጭፍራ የእርሱን ታላቆች ገድለዋቸው ነበርና። የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ።
2. አካዝያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው አርባ ሁለት ዓመት ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ጎቶሊያ የተባለች የዘንበሪ ልጅ ነበረች።
3. እናቱም ክፉ ለማድረግ ትመክረው ነበርና እርሱ ደግሞ በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ።
4. አባቱም ከሞተ በኋላ የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ እስኪጠፉ ድረስ መካሪዎች ነበሩትና።
5. በምክራቸውም ሄደ፥ ከእስራኤልም ንጉሥ ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገለአድ ሊዋጋ ሄደ፤ ሶርያውያንም ኢዮራንም አቈሰሉት።
6. ከሶርያም ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ፤ ታምሞም ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ የአክዓብን ልጅ ኢዮራምን ያይ ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።
7. አካዝያስም ወደ ኢዮራም በመምጣቱ ይጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበረ፤ በመጣም ጊዜ ከኢዮራም ጋር እግዚአብሔር የአክዓብን ቤት ያጠፋ ዘንድ ወደ ቀባው ወደ ናሜሲ ልጅ ወደ ኢዩ ወጣ።
8. ኢዩም በአክዓብ ቤት ላይ ፍርድን ሲፈጽም የይሁዳን መሳፍንትና አካዝያስን ያገለግሉ የነበሩትን የአካዝያስን ወንድሞች ልጆች አግኝቶ ገደላቸው።
9. አካዝያስንም ፈለገው፥ በሰማርያ ተሸሽጎ ሳለ አገኙት፤ ወደ ኢዩም አምጥተው ገደሉትና። በፍጹም ልብ እግዚአብሔርን የፈለገው የኢዮሣፍጥ ልጅ ነው ብለው ቀበሩት። ከአካዝያስም ቤት ማንም መንግሥትን ይይዝ ዘንድ የሚችል አልነበረም።
10. የአካዝያስም እናት ጎቶሊያ ልጅዋ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የይሁዳን ቤተ መንግሥት ዘር ሁሉ አጠፋች።
11. የንጉሡ ልጅ ዮሳቤት ግን ከተገደሉት ከንጉሡ ልጆች መካከል የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሰርቃ ወሰደች፤ እርሱንና ሞግዚቱን በእልፍኝ ውስጥ አኖረቻቸው፤ ጎቶሊያ እንዳታስገድለው የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዛያስ እኅት የካህኑ የዮዳሄ ሚስት ዮሳቤት እንዲሁ ሸሸገችው።
12. በእነርሱም ዘንድ ተሸሽጎ በእግዚአብሔር ቤት ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ፤ ጎቶልያም በምድር ላይ ነገሠች።

  2Chronicles (22/36)