| ← 2Chronicles (21/36) → |
| 1. | ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮራም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |
| 2. | ለእርሱም የኢዮሣፍጥ ልጆች ዓዛርያስ፥ ይሒኤል፥ ዘካርያስ፥ ዔዛርያስ፥ ሚካኤል፥ ሰፋጥያስ የሚባሉ ወንድሞች ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ። |
| 3. | አባታቸውም ብዙ ስጦታ፥ ብርና ወርቅ፥ የከበረም ዕቃ፥ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሰጣቸው፤ መንግሥቱን ግን በኵር ልጁ ስለ ሆነ ለኢዮራም ሰጠ። |
| 4. | ኢዮራምም በአባቱ መንግሥት ላይ ተነሥቶ በጸና ጊዜ ወንድሞቹን ሁሉ ሌሎችንም የእስራኤልን መሳፍንት በሰይፍ ገደለ። |
| 5. | ኢዮራምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ። |
| 6. | የአክአብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። |
| 7. | ነገር ግን ከዳዊት ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን፥ ለእርሱና ለልጆቹም በዘመናት ሁሉ መብራት ይሰጠው ዘንድ ስለ ሰጠው ተስፋ፥ እግዚአብሔር የዳዊትን ቤት ያጠፋ ዘንድ አልወደደም። |
| 8. | በእርሱም ዘመን ኤዶምያስ በይሁዳ ላይ ዐመፀ፥ ለራሱም ንጉሥ አነገሠ። |
| 9. | ኢዮራምም ከአለቆቹና ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስን ሰዎች መታ። |
| 10. | ኤዶምያስ ግን በይሁዳ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፀ፥ በዚያንም ዘመን ልብና ደግሞ በእርሱ ላይ ዐመፀ፥ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ትቶ ነበርና። |
| 11. | ዳግምም በይሁዳ ተራሮች ላይ መስገጃዎችን ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን እንዲያመነዝሩ አደረጋቸው፥ ይሁዳንም አሳተው። |
| 12. | ከነቢዩም ከኤልያስ እንዲህ የሚል ጽሕፈት መጣባት። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በአባትህ በኢዮሣፍጥ መንገድ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህምና፥ |
| 13. | በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ግን ሄደሃልና፥ የአክዓብም ቤት እንዳደረገ ይሁዳንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እንዲያመነዝሩ አድርገሃልና፥ ከአንተም የሚሻሉትን የአባትህን ቤት ወንድሞችህን ገድለሃልና፥ |
| 14. | እነሆ፥ እግዚአብሔር ሕዝብህንና ልጆችህን ሚስቶችህንም ያለህንም ሁሉ በታላቅ መቅሠፍት ይቀሥፋል። |
| 15. | አንተም ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀትህ በየዕለቱ እስኪወጣ ድረስ በክፉ የአንጀት ደዌ ትታመማለህ። |
| 16. | እግዚአብሔርን የፍልስጥኤማውያንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩትን የዓረባውያንን መንፈስ በኢዮራም ላይ አስነሣ። |
| 17. | ወደ ይሁዳም ወጡ፥ አፈረሱአትም፥ የንጉሡንም ቤት ዕቃ ሁሉ፥ ወንዶች ልጆቹንም ሴቶች ልጆቹንም ማረኩ፤ ከታናሹም ልጅ ከአካዝያስ በቀር ልጅ አልቀረለትም። |
| 18. | ከዚህም ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር በማይፈወስ ደዌ አንጀቱን ቀሰፈው። |
| 19. | ከቀንም ወደ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ አንጀቱ ወጣ፥ በክፉም ደዌ ሞተ። ሕዝቡም ለአባቶቹ ያደርገው እንደ ነበር ለእርሱ የመቃብር ወግ አላደረገም። |
| 20. | መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ፤ ማንም ሳያዝንለት ሄደ፤ በዳዊትም ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። |
| ← 2Chronicles (21/36) → |