← 2Chronicles (20/36) → |
1. | እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ በኋላ የሞዓብና የአሞን ልጆች ከእነርሱም ጋር ምዑናውያን ኢዮሣፍጥን ሊወጉ መጡ። |
2. | ወሬኞችም መጥተው። ከባሕሩ ማዶ ከሶሪያ ታላቅ ሠራዊት መጥቶብሃል፤ እነሆም፥ ዓይንጋዲ በተባለች በሐሴሶን ታማር ናቸው ብለው ለኢዮሣፍጥ ነገሩት። |
3. | ኢዮሣፍጥም ፈራ፥ እግዚአብሔርንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና፤ በይሁዳም ሁሉ ጾም አወጀ። |
4. | ይሁዳም እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ተከማቸ፤ ከይሁዳ ከተሞችም ሁሉ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ መጡ። |
5. | ኢዮሣፍጥም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በአዲሱ አደባባይ ፊት ቆመ፤ |
6. | እንዲህም አለ። አቤቱ የአባቶቻችን አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን? የአሕዛብንስ መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኃይልና ችሎታ በእጅህ ነው፥ ሊቋቋምህም የሚችል የለም። |
7. | አምላካችን ሆይ፥ በዚህ ምድር የነበሩትን አሕዛብ ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት ያሳደድህ፥ ለወዳጅህም ለአብርሃም ዘር ለዘላለም የሰጠሃት አንተ አይደለህምን? |
8. | እነርሱም የተቀመጡባት፥ ለስምህም መቅደስን ሠርተውባት። |
9. | ክፉ ነገር፥ የፍርድ ሰይፍ ወይም ቸነፈር ወይም ራብ፥ ቢመጣብን ስምህ ባለበት በዚህ ቤት ፊትና በፊትህ ቆመን በመከራችን ወደ አንተ እንጮኻለን፥ አንተም ሰምተህ ታድነናለህ አሉ። |
10. | አሁንም፥ እነሆ፥ እስራኤል ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ ያልፉባቸው ዘንድ ያልፈቀድህላቸው፥ ነገር ግን ፈቀቅ ብለው ያላጠፉአቸው፥ የአሞንና የሞዓብ ልጆች የሴይርም ተራራ ሰዎች፥ |
11. | እነሆ፥ ለወሮታችን ክፋት ይመልሱልናል፤ ከሰጠኸንም ርስት ያወጡን ዘንድ መጥተዋል። |
12. | አምላካችን ሆይ፥ አንተ አትፈርድባቸውምን? ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን እንቃወም ዘንድ አንችልም፤ የምናደርገውንም አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው። |
13. | የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውም ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር። |
14. | የእግዚአብሔርም መንፈስ ከአሳፍ ወገን በነበረው በሌዋዊው በማታንያ ልጅ በይዒኤል ልጅ በበናያስ ልጅ በዘካሪያስ ልጅ በየሕዚኤል ላይ በጉባኤው መካከል መጣ፤ |
15. | እንዲህም አለ። ይሁዳ ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ፥ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል። ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። |
16. | ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነሆ፥ በጺጽ ዓቀበት ይወጣሉ፤ በሸለቆውም መጨረሻ በይሩኤል ምድረ በዳ ፊት ለፊት ታገኙአቸዋላችሁ። |
17. | እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተሰለፉ፥ ዝም ብላችሁ ቁሙ፥ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥ ነገም ውጡባቸው። |
18. | ኢዮሣፍጥም በምድር ላይ ተደፋ ይሁዳም ሁሉ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። |
19. | ሌዋውያንም፥ የቀዓት ልጆችና የቆሬ ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በእጅግ ታላቅ ድምፅ ያመሰገኑት ዘንድ ቆሙ። |
20. | ማልደውም ተነሡ፥ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና። ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሰላላችኋል አለ። |
21. | ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን። ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉትንም፥ ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። |
22. | ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ። |
23. | የአሞንና የሞዓብ ልጆችም በሴይር ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እያንዳንዱ ባልንጀራውን ለማጥፋት ተረዳዳ። |
24. | የይሁዳም ሰዎች ወደ ምድረ በዳ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፥ ያመለጠም ሰው አልነበረም። |
25. | ኢዮሣፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ይወስዱ ዘንድ መጡ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃም፥ ልብስም፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፥ በዘበዙትም፥ ሁሉንም ይሸከሙ ዘንድ አልቻሉም፤ ከምርኮውም ብዛት የተነሣ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ይበዘብዙ ነበር። |
26. | በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፥ በዚያም እግዚአብሔርን ባረኩ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ። |
27. | የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች፥ በፊታቸውም ኢዮሣፍጥ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ዘንድ ተመለሱ። |
28. | በበገናም በመሰንቆም በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገቡ። |
29. | እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ፍርሃት ሆነ። |
30. | የኢዮሣፍጥም መንግሥት ጸጥ አለች፥ አምላኩም በዙሪያው ካሉ አሳረፈው። |
31. | ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜም የሠላሳ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሀያ አምስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች። |
32. | በአባቱም በአሳ መንገድ ሄደ፥ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔር ፊት ቅን አደረገ። |
33. | ነገር ግን የኮረብታው መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና ልባቸውን ወደ አባቶቻቸው አምላክ አላዘጋጁም ነበር። |
34. | የቀረውም የፊተኛውና የኋለኛው የኢዮሣፍጥ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው በአናኒ ልጅ በኢዩ ታሪክ ተጽፎአል። |
35. | ከዚህም በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሥራው እጅግ ክፉ ከሆነ ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ተባበረ። |
36. | ወደ ተርሴስም የሚሄዱትን መርከቦች ያሠሩ ዘንድ አንድ ሆኑ፤ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር አሠሩ። |
37. | የመሪሳም ሰው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር። ከአካዝያስ ጋር ተባብረሃልና እግዚአብሔር ሥራህን አፍርሶታል ብሎ በኢዮሣፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረ። መርከቦቹም ተሰበሩ፥ ወደ ተርሴስም ይሄዱ ዘንድ አልቻሉም። |
← 2Chronicles (20/36) → |