← 2Chronicles (2/36) → |
1. | ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስም ቤት፥ ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ አሰበ። |
2. | ሰሎሞንም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ ከተራሮችም የሚጠርቡትን ሰማኒያ ሺህ፥ በእነርሱም ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰዎች ቈጠረ። |
3. | ሰሎሞንም እንዲህ ሲል ወደ ጢሮስ ንጉሥ ወደ ኪራም ላከ። ከአባቴ ከዳዊት ጋር እንዳደረግህ፥ የሚቀመጥበትንም ቤት ይሠራ ዘንድ የዝግባ እንጨት እንደ ሰደድህለት፥ እንዲሁ ለእኔ አድርግ። |
4. | እነሆ፥ ለእስራኤል ለዘላለም እንደ ታዘዘው በእግዚአብሔር ፊት የጣፋጩን ሽቱ ለማጠን፥ የገጹንም ኅብስት ለማኖር፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም በመባቻዎቹም በአምላካችንም በእግዚአብሔር በዓላት ለማቅረብ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራና እቀድስ ዘንድ አሰብሁ። |
5. | አምላካችንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ታላቅ ነውና የምሠራው ቤት ታላቅ ነው። |
6. | ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ ይይዘው ዘንድ አይችልምና ለእርሱ ቤት ይሠራ ዘንድ ማን ይችላል? በፊቱ ዕጣን ከማጠን በቀር ቤት እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ? |
7. | አሁንም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው በእኔ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ካሉት ብልሃተኞች ጋር የሚሆን፥ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንና ብረቱን፥ ሐምራዊውንና ቀዩን ሰማያዊውንም ግምጃ የሚሠራ፥ ቅርጽንም የሚያውቅ ብልሃተኛ ሰው ላክልኝ። |
8. | ደግሞም ባሪያዎችህ ከሊባኖስ እንጨት መቍረጥ እንዲያውቁ እኔ አውቃለሁና ከሊባኖስ የዝግባና የጥድ የሰንደልም እንጨት ስደድልኝ። |
9. | የምሠራውም ቤት እጅግ ታላቅና ድንቅ ይሆናልና ብዙ እንጨት ያዘጋጁልኝ ዘንድ፥ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋር ይሆናሉ። |
10. | እነሆም፥ እንጨቱን ለሚቈርጡ ለባሪያዎችህ ሀያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ የተበጠረ ስንዴ፥ ሀያ ሺህም የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ ሀያ ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ። |
11. | የጢሮስ ንጉሥም ኪራም። እግዚአብሔር ሕዝቡን ወድዶአልና በላያቸው አነገሠህ ብሎ ለሰሎሞን መልእክት ላከ። |
12. | ኪራምም ደግሞ አለ። ሰማይንና ምድርን የፈጠረ፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለመንግሥቱም ቤት ይሠራ ዘንድ ጥበበኛና ብልሃተኛ አስተዋይም ልጅ ለንጉሡ ለዳዊት የሰጠ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን። |
13. | አሁንም ከብልሃተኞችህ ጋር ከጌታዬም ከአባትህ ከዳዊት ብልሃተኞች ጋር ይሆን ዘንድ ኪራምአቢ የሚባል ብልሃተኛና አስተዋይ ሰው ሰድጄልሃለሁ። |
14. | እናቱ ከዳን ልጆች ናት፥ አባቱም የጢሮስ ሰው ነው፤ ወርቁንና ብሩንም፥ ናሱንና ብረቱን፥ ድንጋይንና እንጨቱን፥ ሐምራዊውንና ሰማያዊውን ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ ይሠራ ዘንድ፥ ቅርጽም ሌላም ነገር ሁሉ ያደርግ ዘንድ ያውቃል። |
15. | አሁንም ጌታዬ የተናገረውን ስንዴውንና ገብሱን ዘይቱንና የወይን ጠጁን ወደ ባሪያዎቹ ይስደድ፤ |
16. | እኛም ከሊባኖስ የምትሻውን ያህል እንጨት እንቈርጣለን፥ በታንኳም አድርገን በባሕር ላይ ወደ አንተ ወደ ኢዮጴ እንሰድዳለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ። |
17. | ሰሎሞንም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ አባቱ ዳዊት እንደ ቈጠራቸው ቈጠረ፤ መቶ አምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ተገኙ። |
18. | ከእነርሱም የሚሸከሙትን ሰባ ሺህ፥ በተራሮችም ላይ የሚጠርቡትን ሰማንያ ሺህ፥ በሕዝቡም ሥራ ላይ የተሾሙትን ሦስት ሺህ ስድስት መቶ አደረገ። |
← 2Chronicles (2/36) → |