| ← 2Chronicles (19/36) → |
| 1. | የይሁዳም ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ቤቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደኅና ተመለሰ። |
| 2. | ባለ ራእዩ የአናኒ ልጅ ኢዩ ሊገናኘው ወጣ፥ ንጉሡንም ኢዮሣፍጥን። ከሐዲውን ታግዛለህን? ወይስ እግዚአብሔርን የሚጠሉትን ትወድዳለህን? ስለዚህም ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ቍጣ ሆኖብሃል። |
| 3. | ነገር ግን የማምለኪያ ዐፀዶቹን ከምድር አስወግደሃልና፥ እግዚአብሔርንም ትፈልግ ዘንድ ልብህን አዘጋጅተሃልና መልካም ነገር ተገኝቶብሃል አለው። |
| 4. | ኢዮሣፍጥም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ ደግሞም ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ተራራማው እስከ ኤፍሬም አገር ድረስ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ እግዚአብሔር መለሳቸው። |
| 5. | በምድር ላይ በተመሸጉት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ፈራጆች አኖረ። |
| 6. | ፈራጆቹንም። ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አትፈርዱምና፥ እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ተመልከቱ። |
| 7. | አሁንም እግዚአብሔርን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ዘንድ በደልና ለሰው ፊት ማድላት መማለጃም መውሰድ የለምና ሁሉን ተጠንቅቃችሁ አድርጉ አላቸው። |
| 8. | ኢዮሣፍጥም ከሌዋውያንና ከካህናት ከእስራኤልም የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ በእግዚአብሔር ስም ፍርድን እንዲፈርዱ ክርክርንም እንዲቈርጡ በኢየሩሳሌም ሾመ። እነርሱም በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። |
| 9. | እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እንዲሁ እግዚአብሔርን በመፍራት በቅንነትም በፍጹምም ልብ አድርጉ። |
| 10. | በከተሞቻቸውም ከተቀመጡት ከወንድሞቻችሁ በደምና በደም መካከል በሕግና በትእዛዝ በሥርዓትና በፍርድም መካከል ያለ ማናቸውም ነገር ወደ እናንተ ቢመጣ እግዚአብሔርን እንዳይበድሉ፥ ቍጣም በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ እንዳይመጣ አስጠንቅቁአቸው፤ እንዲህም ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም። |
| 11. | እነሆም፥ ለእግዚአብሔር በሚሆነው ነገር ሁሉ የካህናቱ አለቃ አማርያ፥ በንጉሡም ነገር ሁሉ የይሁዳ ቤት አለቃ የይስማኤል ልጅ ዝባድያ በላያችሁ ተሾመዋል፤ ሌዋውያኑም ደግሞ በፊታችሁ አለቆች ይሆናሉ፤ በርትታችሁም አድርጉ፥ እግዚአብሔርም መልካም ከሚያደርግ ጋር ይሁን። |
| ← 2Chronicles (19/36) → |