| ← 2Chronicles (18/36) → |
| 1. | ለኢዮሣፍጥም ብዙ ብልጥግናና ክብር ነበረው፤ ለአክዓብም ጋብቻ ሆነ። |
| 2. | ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችንና በሬዎችን አረደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ይሄድ ዘንድ አባበለው። |
| 3. | የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን? አለው። እርሱም እኔ እንደ አንተ ነኝ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በሰልፍም ከአንተ ጋር እንሆናለን ብሎ መለሰለት። |
| 4. | ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው። |
| 5. | የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቱን አራት መቶ ሰዎች ሰብስቦ። ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር? አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ አሉት። |
| 6. | ኢዮሣፍጥ ግን። እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔርን ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን? አለ። |
| 7. | የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁል ጊዜ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይነግርልኝምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው አለው። ኢዮሳፍጥም። ንጉሥ እንዲህ አይበል አለው። |
| 8. | የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ። የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው አለው። |
| 9. | የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማሪያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። |
| 10. | የክንዓና ልጅ ሰዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሶሪያውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋለህ አለ። |
| 11. | ነቢያትም ሁሉ። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን እያሉ እንዲሁ ትንቢት ይናገሩ ነበር። |
| 12. | ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ። እነሆ፥ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካም ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ አለው። |
| 13. | ሚክያስም። ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ አለ። |
| 14. | ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ። ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር? አለው። እርሱም። ውጣ፥ ተከናወን፤ በእጅህም አልፈው ይሰጣሉ አለ። |
| 15. | ንጉሡም። በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ? አለው። |
| 16. | እርሱም። እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም። ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ ብሎ ተናገረ። |
| 17. | የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝም አላልሁህምን? አለው። |
| 18. | ሚክያስም አለ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። |
| 19. | እግዚአብሔርም። ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን የሚያታልል ማን ነው? አለ። አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። |
| 20. | መንፈስም መጣ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ። እኔ አታልለዋለሁ አለ። እግዚአብሔርም። በምን? አለው። |
| 21. | እርሱም። ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ታታልለዋለህ፤ ይቀናሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ አለ። |
| 22. | አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል። |
| 23. | የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም በጥፊ መታውና። የእግዚአብሔር መንፈስ ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ? አለ። |
| 24. | ሚክያስም። እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ ስትሄድ ታያለህ አለ። |
| 25. | የእስራኤልም ንጉሥ። ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም አለቃ ወደ አሞን፥ ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ። |
| 26. | ንጉሡ እንዲህ ይላል። በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉ አለ። |
| 27. | ሚክያስም። በደህና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም አለ። ደግሞም። እናንተ ሕዝብ ሁሉ፥ ስሙኝ አለ። |
| 28. | የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። |
| 29. | የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን። ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፥ ወደ ሰልፍም ገቡ። |
| 30. | የሶርያም ንጉሥ የሰረገሎቹን አለቆች። ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትጋጠሙ ብሎ አዝዞ ነበር። |
| 31. | የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ። የእስራኤል ንጉሥ ነው አሉ፥ ሊጋጠሙትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ረዳው፥ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው። |
| 32. | የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። |
| 33. | አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳምባውን ወጋው። ሰረጋለኛውንም። ተወግቻለሁና እጅህን ግታ ከሰልፍም ውስጥ አውጣኝ አለው። |
| 34. | በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶሪያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሰረገላው ላይ ራሱን ይደግፍ ነበር፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሞተ። |
| ← 2Chronicles (18/36) → |