| ← 2Chronicles (17/36) → |
| 1. | በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮሳፍጥ ነገሠ፥ በእስራኤልም ላይ ጠነከረ። |
| 2. | በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ወታደሮችን አኖረ፥ በይሁዳም አገር አባቱም አሳ በወሰዳቸው በኤፍሬም ከተሞች ዘበኞችን አስቀመጠ። |
| 3. | እግዚአብሔርም ከኢዮሳፍጥ ጋር ነበረ፥ በፊተኛይቱ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄዶአልና፥ በኣሊምንም አልፈለገምና፤ |
| 4. | ነገር ግን የአባቱን አምላክ ፈለገ፥ በትእዛዙም ሄደ፥ የእስራኤልንም ሥራ አልሠራም። |
| 5. | እግዚአብሔርም መንግሥቱን በእጁ አጸና፤ ይሁዳም ሁሉ እጅ መንሻ ለኢዮሳፍጥ አመጣ፤ እጅግም ብዙ ብልጥግናና ክብር ሆነለት። |
| 6. | ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ ከፍ ከፍ አለ፤ የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ ዐፀዱንም ከይሁዳ አስወገደ። |
| 7. | በነገሠም በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች ያስተምሩ ዘንድ መሳፍንቱን፥ ቤንኃይልን፥ አብድያስን፥ ዘካርያስን፥ ናትናኤልን፥ ሚክያስን፥ ሰደደ። |
| 8. | ከእነርሱም ጋር ሌዋውያንን ሸማያን፥ ነታንያን፥ ዝባድያን፥ አሣሄልን፥ ሰሚራሞትን፥ ዮናትንን፥ አዶንያስን፥ ጦብያን፥ ጦባዶንያን ሰደደ ከእነርሱም ጋር ካህናቱን ኤሊሳማንና ኢዮራምን ሰደደ። |
| 9. | እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በይሁዳ ያስተምሩ ነበር፤ ወደ ይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሄደው ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር። |
| 10. | በይሁዳም ዙሪያ በነበሩ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድንጋጤ ሆነ፥ ከኢዮሳፍጥም ጋር አልተዋጉም። |
| 11. | ከፍልስጥኤማውያን ለኢዮሳፍጥ እጅ መንሻና የብር ግብር ያመጡ ነበር፤ ዓረባውያንም ደግሞ ከመንጎቻቸው ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ በጎችና ሰባት ሺህ ሰባት ሺህ ሰባት መቶ አውራ ፍየሎች ያመጡለት ነበር። |
| 12. | ኢዮሳፍጥም እየበረታና እጅግም እየከበረ ሄደ፤ በይሁዳም ግንቦችንና የጎተራ ከተሞችን ሠራ። |
| 13. | በይሁዳም ከተሞች ብዙ ሥራ ሠራ፥ በኢየሩሳሌምም ጽኑዓን ኃያላን ሰልፈኞች ነበሩት። |
| 14. | ቍጥራቸውም እንደ አባቶቻቸው ቤት ይህ ነበረ፤ ከይሁዳ ሻለቆች አለቃው ዓድና፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ |
| 15. | ከእርሱም በኋላ አለቃው ይሆሐናን፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ |
| 16. | ከእርሱም በኋላ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የቀደሰ የዝክሪ ልጅ ዓማስያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ። |
| 17. | ከብንያምም ጽኑዕ ኃያል የነበረው ኤሊዳሄ፥ ከእርሱም ጋር ቀስትና ጋሻ የሚይዙ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ |
| 18. | ከእርሱም በኋላ ዮዛባት፥ ከእርሱም ጋር ለሰልፍ የተዘጋጁ መቶ ሰማኒያ ሺህ ሰዎች ነበሩ። |
| 19. | ንጉሡ በተመሸጉ በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ካኖራቸውም ሌላ እነዚህ ንጉሡን ያገለግሉ ነበር። |
| ← 2Chronicles (17/36) → |