| ← 2Chronicles (15/36) → |
| 1. | የእግዚአብሔርም መንፈስ በዖዴድ ልጅ በዓዛርያስ ላይ ሆነ፤ |
| 2. | አሳንም ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው። አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል። |
| 3. | እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር። |
| 4. | በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት። |
| 5. | በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረም፥ በምድርም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ነበረ። |
| 6. | እግዚአብሔር በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸው ነበርና ወገን ከወገን ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር። |
| 7. | እናንተ ግን ለሥራችሁ ብድራት ይሆንላችኋልና በርቱ፥ እጃችሁም አይላላ። |
| 8. | አሳም ይህን ቃልና የነቢዩን የዖዴድን ትንቢት በሰማ ጊዜ ልቡ ጸና፥ ከይሁዳና ከቢንያምም አገር ሁሉ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ከያዛቸው ከተሞች ጸያፉን ነገር አስወገደ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ፊት የነበረውን የእግዚአብሔርን መሠዊያ አደሰ። |
| 9. | አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ነበርና እርሱ ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ፥ ከኤፍሬምና ከምናሴም ከስምዖንም መጥተው ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትን ሰበሰበ። |
| 10. | አሳም በነገሠ በአሥራ አምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። |
| 11. | በዚያም ቀን ካመጡት ምርኮ ሰባት መቶ በሬዎችና ሰባት ሺህ በጎች ለእግዚአብሔር ሠዉ። |
| 12. | በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ |
| 13. | የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን የማይፈልግ፥ ታናሽ ወይም ታላቅ፥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን፥ ይገደል ዘንድ ማሉ። |
| 14. | ለእግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅና በእልልታ፥ በእምቢልታና በቀንደ መለከት ማሉ። |
| 15. | በፍጹምም ልባቸው ምለዋልና፥በፍጹምም ሕሊናቸው ፈልገውታልና፥ እርሱም ተገኝቶላቸዋልና ይሁዳ ሁሉ በመሐላው ደስ አላቸው፤ እግዚአብሔርም በዙሪያቸው ዕረፍት ሰጣቸው። |
| 16. | ንጉሡም አሳ እናቱን መዓካን በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስላደረገች ከእቴጌነትዋ አዋረዳት፤ አሳም ምስልዋን ቈርጦ ቀጠቀጠው፥ በቄድሮንም ወንዝ አጠገብ አቃጠለው። |
| 17. | በኮረብታ ላይ የነበሩትን መስገጃዎች ግን ከእስራኤል አላራቀም፤ ይሁን እንጂ የአሳ ልብ በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ነበረ። |
| 18. | አባቱም የቀደሰውን፥ እርሱም የቀደሰውን ወርቁንና ብሩን፥ ልዩ ልዩውንም ዕቃ ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባ። |
| 19. | አሳም እስከ ነገሠበት እስከ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት ድረስ ሰልፍ አልነበረም። |
| ← 2Chronicles (15/36) → |