← 2Chronicles (13/36) → |
1. | ንጉሡም ኢዮርብዓም በነገሠ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። |
2. | ሦስት ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ የእናቱም ስም ሚካያ ነበረ፥ የገብዓ ሰው የኡርኤል ልጅ ነበረች። |
3. | በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ሰልፍ ነበረ። አብያም የተመረጡትን አራት መቶ ሺህ ኃያላን ሰልፈኞች ይዞ ወደ ሰልፍ ወጣ፤ ኢዮርብዓምም የተመረጡትን ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ይዞ በእርሱ ላይ ተሰለፈ። |
4. | አብያም በተራራማው በኤፍሬም አገር ባለው በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ። ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ |
5. | የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መንግሥትን ለዳዊትና ለልጆቹ በጨው ቃል ኪዳን ለዘላለም እንደ ሰጠ በውኑ አታውቁምን? |
6. | የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባሪያ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን ተነሥቶ በጌታው ላይ ዐመፀ። |
7. | ክፉዎች ሰዎችና ምናምንቴዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሮብዓም ሕፃንና ለጋ በነበረበት ጊዜ፥ ሊቋቋማቸውም ባልቻለበት ጊዜ፥ በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ላይ በረቱበት። |
8. | አሁንም በዳዊት ልጆች እጅ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ ታስባላችሁ። እናንተም እጅግ ታላቅ ሕዝብ ናችሁ፥ ኢዮርብዓምም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁ የወርቅ እምቦሶች ከእናንተ ጋር ናቸው። |
9. | የአሮንን ልጆች የእግዚአብሔርን ካህናትና ሌዋውያን አላሳደዳችሁምን? እንደ ሌሎችም አሕዛብ ልማድ ካህናትን አላደረጋችሁምን? አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ይዞ ይቀድስ ዘንድ የሚመጣ ሁሉ አማልክት ላልሆኑት ለእነዚያ ካህን ይሆናል። |
10. | ለእኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፥ አልተውነውም፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች የአሮን ልጆች ካህናቱ ሌዋውያኑም በሥራቸው ከእኛ ጋር ናቸው። |
11. | በየጥዋቱና በየማታውም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ጣፋጩን ዕጣን ያሳርጋሉ፤ የገጹንም ኅብስት በንጹህ ገበታ ላይ፥ የወርቁን መቅረዝና ቀንዲሎቹንም ማታ ማታ እንዲያበሩ ያዘጋጃሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንጠብቃለን፥ እናንተ ግን ትታችሁታል። |
12. | እነሆም፥ እግዚአብሔር በእኛ ላይ አለቃ ነው፥ መለከቱንም የሚነፉ ካህናቱ ከእኛ ጋር ናቸው፥ በእናንተም ላይ ይጮኻሉ። የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አይበጃችሁምና ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ። |
13. | ኢዮርብዓም ግን ድብቅ ጦር በስተ ኋላቸው አዞረ፤ እነርሱ በይሁዳ ፊት ሆነው ድብቅ ጦሩ በስተ ኋላቸው ነበረ። |
14. | ይሁዳም ወደ ኋላው በተመለከተ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰልፉ በፊቱና በኋላው ነበረ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፥ ካህናቱም መለከቱን ነፉ። |
15. | የይሁዳም ሰዎች ጮኹ፤ የይሁዳም ሰዎች በጮኹ ጊዜ እግዚአብሔር ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት መታቸው። |
16. | የእስራኤልም ልጆች ከይሁዳ ፊት ሸሹ፥ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። |
17. | አብያና ሕዝቡ ታላቅ አመታት መቱአቸው፤ ከእስራኤልም አምስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች ተገድለው ወደቁ። |
18. | በዚያም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፥ የይሁዳም ልጆች በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ታምነው ነበርና አሸነፉ። |
19. | አብያም ኢዮርብዓምን አሳደደው፥ ከእርሱም ከተሞቹን፥ ቤቴልንና መንደሮችዋን፥ ይሻናንና መንደሮችዋን፥ ዔፍሮንንና መንደሮችዋን ወሰደ። |
20. | ኢዮርብዓምም ከዚያ በኋላ በአብያ ዘመን አልበረታም፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው፥ ሞተም። |
21. | አብያም ጸና፥ አሥራ አራትም ሚስቶች አገባ፥ ሀያ ሁለትም ወንዶች ልጆችንና አሥራ ስድስት ሴቶች ልጆችን ወለደ። |
22. | የአብያም የቀረው ነገርና አካሄዱ የተናገራቸውም ቃሎች በነቢዩ በአዶ መጽሐፍ ተጽፈዋል። |
← 2Chronicles (13/36) → |