| 2Chronicles (1/36) → | 
| 1. | የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በመንግሥቱ በረታ፤ አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፥ እጅግም አገነነው። | 
| 2. | ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች፥ ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ተናገረ። | 
| 3. | ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር ጉባኤው ሁሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር መገናኛ ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው የኮረብታ መስገጃ ሄዱ። | 
| 4. | ለእግዚአብሔር ታቦት ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎለት ነበርና ዳዊት ከቂርያትይዓሪም ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር። | 
| 5. | የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንም ጉባኤውም ይህን ይፈልጉት ነበር። | 
| 6. | ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፥ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። | 
| 7. | በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር። ምን እንድሰጥህ ለምነኝ ሲል ለሰሎሞን ተገለጠ። | 
| 8. | ሰሎሞንም እግዚአብሔርን አለው። ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ምሕረት አድርገሃል፥ በእርሱም ፋንታ አንግሠኸኛል። | 
| 9. | አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ቍጥሩ እንደ ምድር ትቢያ በሆነው በብዙ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው ተስፋ ይጽና። | 
| 10. | አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ፤ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ የሚችል የለምና። | 
| 11. | እግዚአብሔርም ሰሎሞንን። ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንና የጠላቶችህን ነፍስ ረጅምም ዕድሜን አልለመንህምና፥ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ለመፍረድ ትችል ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ለራስህ ለምነሃልና ጥበብንና እውቀትን ሰጥቼሃለሁ፤ | 
| 12. | ከአንተ በፊትም ከነበሩት ከአንተም በኋላ ከሚነሡት ነገሥታት አንድ ስንኳ የሚመስልህ እንዳይኖር ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንም እሰጥሃለሁ አለው። | 
| 13. | ሰሎሞንም በገባዖን ካለው ከኮረብታው መስገጃ ከመገናኛው ድንኳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ። | 
| 14. | ሰሎሞንም ሰረገሎቹንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፥ አንድ ሺህም አራት መቶ ሰረገሎች፥ አሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎች ከተሞችና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። | 
| 15. | ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። | 
| 16. | ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር። | 
| 17. | አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ አምሳ ሰቅል ብር ከግብጽ ይወጣ ነበር፤ እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሶሪያ ነገሥታት ሁሉ በእጃቸው ያመጡላቸው ነበር። | 
| 2Chronicles (1/36) → |