← 1Samuel (9/31) → |
1. | ስሙ ቂስ የተባለ አንድ ብንያማዊ ሰው ነበረ፤ እርሱም የአቢኤል ልጅ፥ የጽሮር ልጅ፥ የብኮራት ልጅ፥ የብንያማዊው የአፌቅ ልጅ፥ ጽኑዕ ኃያል ሰው ነበረ። |
2. | ለእርሱም ሳኦል የሚባል የተመረጠ መልካም ልጅ ነበረው፤ ከእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ይልቅ መልካም የሆነ ሰው አልነበረም፤ ከሕዝቡም ሁሉ ይልቅ ከትከሻውና ከዚያም በላይ ቁመቱ ዘለግ ያለ ነበረ። |
3. | የሳኦልም አባት የቂስ አህዮች ጠፍተው ነበር፤ ቂስም ልጁን ሳኦልን። ከብላቴኖቹ አንዱን ወስደህ ተነሣ፥ አህዮችንም ለመሻት ሂድ አለው። |
4. | በተራራማው በኤፍሬም አገርና በሻሊሻ አለፉ፥ አላገኙአቸውምም በሻዕሊም ምድርም አለፉ፥ በዚያም አልነበሩም፤ በብንያም ምድርም አለፉ፥ አላገኙአቸውምም። |
5. | ወደ ጹፍ ምድር በመጡ ጊዜም ሳኦል ከእርሱ ጋር የነበረውን ብላቴና። አባቴ ስለ አህዮች ማሰብ ትቶ ስለ እኛ እንዳይጨነቅ፥ ና፥ እንመለስ አለው። |
6. | እርሱም። እነሆ፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በዚህች ከተማ አለ፤ እርሱም የተከበረ ሰው ነው፥ የሚናገረውም ሁሉ በእውነት ይፈጸማል፤ አሁን ወደዚያ እንሂድ፤ ምናልባት የምንሄድበትን መንገድ ይነግረናል አለው። |
7. | ሳኦልም ብላቴናውን። እነሆ፥ እንሄዳለን፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሰው ምን እናመጣለታለን? እንጀራ ከከረጢታችን አልቆአልና፥ እጅ መንሻም የለንምና ለእግዚአብሔር ሰው የምናመጣለት ምን አለን? አለው። |
8. | ብላቴናው ደግሞ ለሳኦል መልሶ። እነሆ፥ በእጄ የሰቅል ብር ሩቡ አለኝ፤ እርሱንም መንገዳችንን እንዲነግረን ለእግዚአብሔር ሰው እሰጣለሁ አለ። |
9. | ዛሬ ነቢይ የሚባለው ቀድሞ ባለ ራእይ ይባል ነበርና አስቀድሞ በእስራኤል ዘንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሲሄድ። ኑ፥ ወደ ባለ ራእይ እንሂድ ይል ነበር። |
10. | ሳኦልም ብላቴናውን። የተናገረኸው ነገር መልካም ነው፤ ና፥ እንሂድ አለውና የእግዚአብሔር ሰው ወዳለበት ከተማ ሄዱ። |
11. | በከተማይቱም ዳገት በወጡ ጊዜ ቆነጃጅት ውኃውን ሊቀዱ ሲወጡ አገኙና። ባለ ራእይ በዚህ አለ ወይ? አሉአቸው። |
12. | እነርሱም። አዎን፤ እነሆ፥ በፊታችሁ ነው፤ ዛሬ ወደ ከተማይቱ መጥቶአልና፥ ዛሬም ሕዝቡ በኮረብታው ላይ ባለው መስገጃ መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸውና ፈጥናችሁ ውጡ። |
13. | ወደ ከተማይቱም በገባችሁ ጊዜ መሥዋዕቱን እርሱ የሚባርክ ስለ ሆነ እርሱ ሳይወጣ ሕዝቡ ምንም አይቀምሱምና፥ ከዚያም በኋላ የተጠሩት ይበላሉና ለመብላት ወደ ኮረብታው መስገጃ ሳይወጣ ታገኙታላችሁ፤ በዚህም ጊዜ ታገኙታላችሁና አሁን ውጡ አሉአቸው። |
14. | ወደ ከተማይቱም ወጡ፤ በከተማይቱም ውስጥ በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ሳሙኤል ወደ ኮረብታው መስገጃ ለመውጣት ወደ እነርሱ መጣ። |
15. | ገናም ሳኦል ሳይመጣ ከአንድ ቀን በፊት እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ ብሎ ገልጦለት ነበር። |
16. | ነገ በዚህች ሰዓት ከብንያም አገር አንድ ሰው እሰድድልሃለሁ፤ ልቅሶአቸው ወደ እኔ የደረስ ሕዝቤን ተመልክቻለሁና ለሕዝቤ ለእስራኤል አለቃ ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ሕዝቤን ያድናል። |
17. | ሳሙኤልም ሳኦልን ባየ ጊዜ እግዚአብሔር። ያ የነገርሁህ ሰው እነሆ፤ እርሱም በሕዝቤ ላይ ይሠለጥናል አለው። |
18. | ሳኦልም በበሩ ወደ ሳሙኤል ቀርቦ። የባለ ራእዩ ቤት ወዴት እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለው። |
19. | ሳሙኤልም መልሶ ሳኦልን። ባለ ራእዩ እኔ ነኝ፤ ዛሬም ከእኔ ጋር ትበላላችሁና በፊቴ ወደ ኮረብታው መስገጃ ውጡ፤ ነገም አሰናብትሃለሁ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ እነግርሃለሁ፤ |
20. | ከሦስት ቀንም በፊት የጠፉ አህዮችህ ተገኝተዋልና ልብህን አትጣልባቸው። የእስራኤል ምኞት ለማን ነው? ለአንተና ለአባትህ ቤት አይደለምን? አለው። |
21. | ሳኦልም መልሶ። እኔ ከእስራኤል ነገዶች ከሚያንስ ወገን የሆንሁ ብንያማዊ አይደለሁምን? ወገኔስ ከብንያም ነገድ ወገኖች ሁሉ የሚያንስ አይደለምን? እንዲህስ ያለውን ነገር ለምን ነገርኸኝ? አለው። |
22. | ሳሙኤልም ሳኦልንና ብላቴናውን ወስዶ ወደ አዳራሽ አገባቸው፥ በመርፈቂያውም ራስ አስቀመጣቸው፤ የተጠሩትም ሠላሳ ሰዎች ያህል ነበሩ። |
23. | ሳሙኤልም ወጥቤቱን። በአንተ ዘንድ አኑረው ብዬ የሰጠሁህን እድል ፈንታ አምጣ አለው። |
24. | ወጥቤቱም ጭኑንና በእርሱ ላይ የነበረውን አምጥቶ በሳኦል ፊት አኖረው። ሳሙኤልም። ሕዝቡን ከጠራሁ ጀምሮ እስከ ተወሰነው ጊዜ ድረስ ለአንተ ተጠብቆአልና እነሆ፥ የተቀመጠልህን በፊትህ አኑረህ ብላው አለ። በዚያም ቀን ሳኦል ከሳሙኤል ጋር በላ። |
25. | ከኮረብታውም መስገጃ ወደ ከተማይቱ ወረዱ፤ ሳሙኤልም ለሳኦል በሰገነቱ ላይ መኝታ አዘጋጀለት፥ እርሱም ተኛ። |
26. | ማልዶም ተነሡ፤ በነጋም ጊዜ ሳሙኤል ሳኦልን ከሰገነቱ ላይ ጠርቶ። ተነሣና ላሰናብትህ አለው። ሳኦልም ተነሣ፥ እርሱና ሳሙኤልም ሁለቱ ወደ ሜዳ ወጡ። |
27. | እነርሱም በከተማይቱ ዳር ሲወርዱ ሳሙኤል ሳኦልን። ብላቴናውን ወደ ፊታችን እንዲያልፍ እዘዘው፤ አንተ ግን የእግዚአብሔርን ቃል አሰማህ ዘንድ በዚህ ቁም አለው። ብላቴናውም አለፈ። |
← 1Samuel (9/31) → |