← 1Samuel (8/31) → |
1. | እንዲህም ሆነ፤ ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ላይ ፈራጆች አደረጋቸው። |
2. | የበኵር ልጁም ስም ኢዮኤል፥ የሁለተኛውም ስም አብያ ነበረ። እነርሱም በቤርሳቤህ ይፈርዱ ነበር። |
3. | ልጆቹም በመንገዱ አልሄዱም፥ ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር። |
4. | የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና። |
5. | እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት። |
6. | የሚፈርድልንም ንጉሥ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው፤ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። |
7. | እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው። በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ። |
8. | ከግብጽ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው እንግዶች አማልክት በማምለካቸው እንደ ሠሩት ሥራ ሁሉ እንዲሁ በአንተ ደግሞ ያደርጉብሃል። |
9. | አሁንም ቃላቸውን ስማ፤ ነገር ግን ጽኑ ምስክር መስክርባቸው፥ በእነርሱም ላይ የሚነግሠውን የንጉሡን ወግ ንገራቸው። |
10. | ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ንጉሥን ለፈለጉ ሕዝብ ነገራቸው። |
11. | እንዲህም አለ። በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፥ በሰረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ፤ |
12. | ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ይሆናሉ። |
13. | ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቶ ቀማሚዎችና ወጥቤቶች አበዛዎችም ያደርጋቸዋል። |
14. | ከእርሻችሁና ከወይናችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። |
15. | ከዘራችሁና ከወይናችሁም አሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። |
16. | ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል። |
17. | ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ። |
18. | በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አልሰማችሁም። |
19. | ሕዝቡ ግን የሳሙኤልን ነገር ይሰማ ዘንድ እንቢ አለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይሁንልን፥ |
20. | እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፥ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል አሉት። |
21. | ሳሙኤልም የሕዝቡን ቃል ሁሉ ሰማ፥ ለእግዚአብሔርም ተናገረ። |
22. | እግዚአብሔርም ሳሙኤልን። ቃላቸውን ስማ፥ ንጉሥም አንግሥላቸው አለው። ሳሙኤልም የእስራኤልን ሰዎች። እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ሂዱ አላቸው። |
← 1Samuel (8/31) → |