← 1Samuel (7/31) → |
1. | የቂርያትይዓሪም ሰዎችም መጥተው የእግዚአብሔርን ታቦት አወጡ፥ በኮረብታውም ላይ ወዳለው ወደ አሚናዳብ ቤት አገቡት፤ የእግዚአብሔርም ታቦት እንዲጠብቅ ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት። |
2. | ታቦቱም በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ ወራቱ ረዘመ፥ ሀያ ዓመትም ሆነ፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ አዝኖ እግዚአብሔርን ተከተለ። |
3. | ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ። በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ እንግዶችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር አቅኑ፥ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ያድናችኋል ብሎ ተናገራቸው። |
4. | የእስራኤልም ልጆች በኣሊምንና አስታሮትን አራቁ፥ እግዚአብሔርንም ብቻ አመለኩ። |
5. | ሳሙኤልም። እስራኤልን ሁሉ ወደ ምጽጳ ሰብስቡ፥ ስለ እናንተም ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ አለ። |
6. | ወደ ምጽጳም ተሰበሰቡ፤ ውኃም ቀድተው በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሱ፥ በዚያም ቀን ጾሙ፥ በዚያም። እግዚአብሔርን በድለናል አሉ። ሳሙኤልም በእስራኤል ልጆች ላይ በምጽጳ ፈረደ። |
7. | ፍልስጥኤማውያንም የእስራኤል ልጆች ወደ ምጽጳ እንደ ተሰበሰቡ በሰሙ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን አለቆች በእስራኤል ላይ ወጡ፤ የእስራኤልም ልጆች ሰምተው ፍልስጥኤማውያንን ፈሩ። |
8. | የእስራኤልም ልጆች ሳሙኤልን። ከፍልስጥኤማውያን እጅ ያድነን ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ትጸልይልን ዘንድ አትታክት አሉት። |
9. | ሳሙኤልም አንድ የሚጠባ የበግ ጠቦት ወስዶ ለእግዚአብሔር ፈጽሞ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው፤ ሳሙኤልም ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው። |
10. | ሳሙኤልም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሲያሳርግ ፍልስጥኤማውያን ከእስራኤል ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በዚያች ቀን በፍልስጥኤማውያን ላይ ታላቅ ነጐድጓድ አንጐደጐደ፥ አስደነገጣቸውም በእስራኤልም ፊት ድል ተመቱ። |
11. | የእስራኤልም ሰዎች ከምጽጳ ወጡ፥ ፍልስጥኤማውያንንም አሳደዱ፤ በቤትካር ታችም እስኪደርሱ ድረስ መቱአቸው። |
12. | ሳሙኤልም አንድ ድንጋይ ወስዶ በምጽጳና በሼን መካከል አኖረው፤ ስሙንም። እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶናል ሲል አቤንኤዘር ብሎ ጠራው። |
13. | ፍልስጥኤማውያንም ተዋረዱ፥ ዳግመኛም ከዚያ ወዲያ ወደ እስራኤል ድንበር አልወጡም፤ በሳሙኤል ዕድሜ ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ በፍልስጥኤማውያን ላይ ነበረች። |
14. | ፍልስጥኤማውያንም ከአስቀሎና ጀምሮ እስከ ጌት ድረስ ከእስራኤል የወሰዱአቸው ከተሞች ለእስራኤል ተመለሱ፤ እስራኤልም ድንበሩን ከፍልስጥኤማውያን እጅ አዳነ። በእስራኤልና በአሞራውያንም መካከል ዕርቅ ነበረ። |
15. | ሳሙኤልም በዕድሜው ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። |
16. | በየዓመቱም ወደ ቤቴል ወደ ጌልገላ ወደ ምጽጳም ይዞር ነበር፤ በእነዚያም ስፍራዎች ሁሉ በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር። |
17. | ቤቱም በዚያ ነበረና ወደ አርማቴም ይመለስ ነበር፤ በዚያም በእስራኤል ላይ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ። |
← 1Samuel (7/31) → |