1Samuel (6/31)  

1. የእግዚአብሔር ታቦት በፍልስጥኤማውያን አገር ሰባት ወር ተቀመጠ።
2. ፍልስጥኤማውያንም ካህናትንና ምዋርተኞችን ጠርተው። በእግዚአብሔር ታቦት ላይ ምን እናድርግ? ወደ ስፍራውስ በምን እንስደደው? አስታውቁን አሉ።
3. እነርሱም። የእስራኤልን አምላክ ታቦት ብትሰድዱ የበደል መሥዋዕት መልሱለት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፥ የዚያን ጊዜም ትፈወሳላችሁ፤ እጁም ከእናንተ አለመራቁ ስለ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ አሉ።
4. እነርሱም። ስለ በደል መሥዋዕት የምንመልስለት ምንድር ነው? አሉ። እነርሱም እንዲህ አሉ። እናንተንና አለቆቻችሁን ያገኘች መቅሠፍት አንዲት ናትና እንደ ፍልስጥኤማውያን አለቆች ቍጥር አምስት የወርቅ እባጮች አምስትም የወርቅ አይጦች አቅርቡ።
5. የእባጫችሁንም ምሳሌ፥ ምድራችሁንም የሚያጠፋአትን የአይጦችን ምሳሌ አድርጋችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብርን ስጡ፤ እጁን ከእናንተና ከአማልክቶቻችሁ ከምድራችሁም ምናልባት ያቀልል ይሆናል።
6. ግብጻውያንና ፈርዖንም ልባቸውን እንዳጸኑ ልባችሁን ለምን ታጸናላችሁ? እግዚአብሔር ኃይሉን ካደረገባቸው በኋላ ያወጡአቸው አይደሉምን?
7. እነርሱም አልሄዱምን? አሁንም ወስዳችሁ አንዲት ሰረገላ ሥሩ፤ የሚያጠቡም፥ ቀንበር ያልተጫነባቸውን ሁለት ላሞች በሰረገላ ጥመዱአቸው፥ እንቦሶቻቸውንም ለይታችሁ ወደ ቤት መልሱአቸው።
8. የእግዚአብሔርንም ታቦት ወስዳችሁ በሰረገላው ላይ አኑሩት፤ ስለ በደልም መሥዋዕት ያቀረባችሁትን የወርቁን ዕቃ በሣጥን ውስጥ አድርጋችሁ በታቦቱ አጠገብ አኑሩት፤ ይሄድም ዘንድ ስደዱት።
9. ተመልከቱም በድንበሩም መንገድ ወደ ቤትሳሚስ ቢወጣ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ያደረገብን እግዚአብሔር ነው፤ አለዚያም እንዲያው መጥቶብናል እንጂ የመታን የእርሱ እጅ እንዳልሆነ እናውቃለን።
10. ሰዎቹም እንዲሁ አደረጉ፤ የሚያጠቡትን ሁለቱን ላሞች ወሰዱ፥ በሰረገላም ጠመዱአቸው፥ እንቦሶቻቸውንም በቤት ዘጉባቸው፤
11. የእግዚአብሔርም ታቦት፥ የወርቁ አይጦችና የእባጮቻቸው ምሳሌ ያሉበትንም ሣጥን በሰረገላው ላይ ጫኑ።
12. ላሞችም ወደ ቤትሳሚስ ወደሚወስደው መንገድ አቅንተው እምቧ እያሉ በጎዳናው ላይ ሄዱ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላሉም፤ የፍልስጥኤማውያንም አለቆች እስከ ቤትሳሚስ ዳርቻ ድረስ በኋላ በኋላቸው ይሄዱ ነበር።
13. የቤትሳሚስ ሰዎችም በሸለቆው ውስጥ ስንዴ ያጭዱ ነበር፤ ዓይናቸውንም ከፍ አድርገው ታቦቱን አዩ፥ በማየታቸውም ደስ አላቸው።
14. ሰረገላውም ወደ ቤትሳሚሳዊው ወደ ኢያሱ እርሻ መጣ፥ ታላቅም ድንጋይ በነበረበት በዚያ ቆመ፤ የሰረገላውንም እንጨት ፈልጠው ላሞቹን ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ።
15. ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት፥ ከእርሱ ጋር የነበረውንም የወርቅ ዕቃ ያለበትን ሣጥን አወረዱ፥ በታላቁም ድንጋይ ላይ አኖሩት፤ በዚያም ቀን የቤትሳሚስ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረቡ፥ መሥዋዕትንም ሠዉ።
16. ፍልስጥኤማውያንም አምስቱ አለቆች ባዩት ጊዜ በዚያው ቀን ወደ አስቀሎና ተመለሱ።
17. ፍልስጥኤማውያን ስለ በደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረቡአቸው የወርቅ እባጮች እነዚህ ናቸው፤ አንዲቱ ለአዛጦን፥ አንዲቱም ለጋዛ፥ አንዲቱም ለአስቀሎና፥ አንዲቱ ለጌት፥
18. አንዲቱ ለአቃሮን የወርቁም አይጦች ቍጥር ለአምስቱ የፍልስጥኤማውያን አለቆች እንደ ነበሩት ከተሞች ሁሉ ቍጥር እንዲሁ ነበረ፤ እነርሱም እስከ ታላቁ ድንጋይ የሚደርሱ ከተሞችና መንደሮች ናቸው። በዚህም ድንጋይ ላይ የእግዚአብሔርን ታቦት አስቀመጡ፥ ድንጋዩም እስከ ዛሬ ድረስ በቤትሳሚሳዊው በኢያሱ እርሻ አለ።
19. ወደ እግዚአብሔርም ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልና የቤትሳሚስን ሰዎች መታ፤ በሕዝቡም ከአምስት ሺህ ሰው ሰባ ሰዎችን መታ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ ግዳይ ስለ መታ ሕዝቡ አለቀሰ።
20. የቤትሳሚስም ሰዎች። በዚህ በቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማን ይችላል? ከእኛስ ወጥቶ ወደ ማን ይሄዳል? አሉ።
21. በቂርያትይዓሪምም ወደ ተቀመጡት ሰዎች መልክተኞች ልከው። ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት መልሰዋል፤ ወርዳችሁም ወደ እናንተ አውጡት አሉ።

  1Samuel (6/31)