← 1Samuel (4/31) → |
1. | እስራኤልም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጋ ወጡ፥ በአቤንኤዘር አጠገብ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያን በአፌቅ ሰፈሩ። |
2. | ፍልስጥኤማውያንም በእስራኤል ላይ ተሰለፉ፤ ሰልፉም በተመደበ ጊዜ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ፊት ተመቱ፤ ጦርነት በተደረገበትም ስፍራ ከእስራኤል አራት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ገደሉ። |
3. | ሕዝቡም ወደ ሰፈር በመጡ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች። ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ፊት ስለ ምን መታን? በመካከላችን እንዲሄዱ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ አሉ። |
4. | ሕዝቡም ወደ ሴሎ ላኩ፥ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዚያ አመጡ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ። |
5. | የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፥ ምድሪቱም አስተጋባች። |
6. | ፍልስጥኤማውያንም የእልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ። በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምንድር ነው? አሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አስተዋሉ። |
7. | ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው። እግዚአብሔር ወደ ሰፈር መጥቶአል አሉ። ደግሞም እንዲህ አሉ። ወዮልን፤ ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር አልሆነም። |
8. | ወዮልን፤ ከእነዚህ ከኃያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብጻውያንን በምድረ በዳ በልዩ በልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው። |
9. | እናንተ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፥ አይዞአችሁ፥ ጎብዙ፤ እናንተ ባሪያዎች እንዳደረጋችኋቸው ዕብራውያን ባሪያዎች እንዳያደርጉአችሁ ጎብዙ፥ ተዋጉ። |
10. | ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፤ እስራኤልም ተመቱ፥ ሁሉም እያንዳንዱ ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፤ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፥ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ። |
11. | የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ። |
12. | በዚያም ቀን አንድ የብንያም ሰው ከሰልፍ እየበረረ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ወደ ሴሎ መጣ። |
13. | በመጣም ጊዜ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ተናውጦ ነበርና በመንገድ ዳር በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር፤ ሰውዮውም ወደ ከተማይቱ ገብቶ ባወራ ጊዜ ከተማይቱ ሁሉ ተጭዋጭዋኸች። |
14. | ዔሊም የጩኸቱን ድምፅ በሰማ ጊዜ። ይህ ጫጫታ ምንድር ነው? አለ። ሰውዮውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው። |
15. | ዔሊም የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ነበረ፤ ዓይኖቹም ማየት እስኪሳናቸው ድረስ ፈዝዘው ነበር። |
16. | ሰውዮውም ዔሊን። ከሰልፍ የመጣሁ እኔ ነኝ፥ ዛሬም ከሰልፍ ኮበለልሁ አለ። እርሱም። ልጄ ሆይ፥ ነገሩሳ እንዴት ሆነ? አለው። |
17. | ወሬኛውም መልሶ። እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ግድያ ሆኖአል፥ ሁለቱም ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማርካለች አለ። |
18. | ሰውዮውም ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ ዔሊ በበሩ አጠገብ ካለው ከወንበሩ ወደቀ፤ እርሱ ሸምግሎ ደንግዞም ነበርና አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም በእስራኤል ላይ አርባ ዓመት ፈራጅ ነበረ። |
19. | ምራቱም የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ታቦት እንደ ተማረከች፥ አማትዋና ባልዋም እንደ ሞቱ በሰማች ጊዜ ምጥ ደርሶባት ነበርና ተንበርክካ ወለደች። |
20. | ወደሞትም በቀረበች ጊዜ በዙሪያዋ ያሉት ሴቶች። ወንድ ልጅ ወልደሻልና አትፍሪ አሉአት። እርስዋ ግን አልመለሰችላቸውም፥ በልብዋም አላኖረችውም። |
21. | እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከች ስለአማትዋና ስለ ባልዋም። ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕፃኑን ስም። ኢካቦድ ብላ ጠራችው። |
22. | እርስዋም። የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለችና ክብር ከእስራኤል ለቀቀ አለች። |
← 1Samuel (4/31) → |