| ← 1Samuel (31/31) |
| 1. | ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ። |
| 2. | ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ። |
| 3. | ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ እርሱም ከቀስተኞቹ የተነሣ እጅግ ተጨነቀ። |
| 4. | ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን። እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይወጉኝና እንዳይሳለቁብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ። |
| 5. | ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወደቀ፥ ከእርሱም ጋር ሞተ። |
| 6. | በዚያም ቀን ሳኦል ሦስቱም ልጆቹ ጋሻ ጃግሬውም ሰዎቹም ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ። |
| 7. | በሸለቆውም ማዶና በዮርዳኖስ ማዶ የነበሩ እስራኤላውያን የእስራኤል ሰዎች እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቹን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው። |
| 8. | በማግሥቱም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው። |
| 9. | የሳኦልንም ራስ ቈረጠው የጦር ዕቃውን ገፍፈው ለጣዖታቱ መቅደስ ለሕዝቡም የምስራች ይሰጥ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ሁሉ ሰደዱ። |
| 10. | የጦር ዕቃውንም በአስታሮት መቅደስ ውስጥ አኖሩት፤ ሬሳውንም በቤትሳን ቅጥር ላይ አንጠለጠሉት። |
| 11. | ፍልስጥኤማውያንም በሳኦል ላይ ያደረጉትን የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች በሰሙ ጊዜ፥ |
| 12. | ጀግኖች ሰዎች ሁሉ ተነሥተው ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ የሳኦልንም ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ከቤትሳን ቅጥር ላይ አወረዱ፤ ወደ ኢያቢስም መጡ፥ በዚያም አቃጠሉት። |
| 13. | አጥንታቸውንም ወሰዱ በኢያቢስም ባለው በአጣጡ ዛፍ በታች ቀበሩት፥ ሰባት ቀንም ጾሙ። |
| ← 1Samuel (31/31) |