← 1Samuel (30/31) → |
1. | እንዲህም ሆነ፤ ዳዊትና ሰዎቹ በሦስተኛው ቀን ወደ ጺቅላግ በመጡ ጊዜ፥ አማሌቃውያን በደቡብ አገርና በጺቅላግ ላይ ዘምተው ነበር፥ ጺቅላግንም መትተው በእሳት አቃጥለዋት ነበር፤ |
2. | ሴቶቹንና በውስጥዋም የነበሩትን ሁሉ ከታናሽ እስከ ታላቅ ድረስ ማርከው ነበር፤ ሁሉንም ወስደው መንገዳቸውን ሄዱ እንጂ አንድስ እንኳ አልገደሉም ነበር። |
3. | ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ከተማ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ በእሳት ተቃጥላ፥ ሚስቶቻቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው አገኙ። |
4. | ዳዊት ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማልቀስ ኃይል እስኪያጡ ድረስ አለቀሱ። |
5. | የዳዊትም ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢግያ ተማርከው ነበር። |
6. | ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻቸው የሕዝቡ ሁሉ ልብ ተቈጥቶ ነበርና ሕዝቡ ሊወግሩት ስለ ተናገሩ ዳዊት እጅግ ተጨነቀ፤ ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ። |
7. | ዳዊትም የአቢሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን። ኤፉዱን አቅርብልኝ አለው፤ አብያታርም ኤፉዱን ለዳዊት አቀረበለት። |
8. | ዳዊትም። የእነዚህን ሠራዊት ፍለጋ ልከተልን? አገኛቸዋለሁን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም። ታገኛቸዋለህና፥ ፈጽመህም ምርኮውን ትመልሳለህና ፍለጋቸውን ተከተል ብሎ መለሰለት። |
9. | ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስት መቶ ሰዎች ሄዱ፥ እስከ ቦሦር ወንዝ ድረስም መጡ፤ ከእነርሱም የቀሩት በዚያ ተቀመጡ። |
10. | ዳዊትም ከእርሱም ጋር ያሉት አራት መቶ ሰዎች አሳደዱ፤ ሁለቱ መቶ ሰዎች ግን የቦሦር ወንዝን መሻገር ደክመዋልና በኋላ ቀሩ። |
11. | በበረሀውም ውስጥ አንድ ግብጻዊ አግኝተው ወደ ዳዊት ይዘውት መጡ፤ እንጀራም ሰጡትና በላ፥ ውኃም አጠጡት፤ |
12. | ከበለሱም ጥፍጥፍ ቁራጭና ሁለት የወይን ዘለላ ሰጡት፤ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንጀራ አልበላም ውኃም አልጠጣም ነበርና በበላ ጊዜ ነፍሱ ወደ እርሱ ተመለሰች። |
13. | ዳዊትም። አንተ የማን ነህ? ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም። እኔ የአማሌቃዊ ባሪያ ግብጻዊ ብላቴና ነኝ፤ ከሦስት ቀንም በፊት ታምሜ ነበርና ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ። |
14. | እኛም በከሊታውያን ደቡብ፥ በይሁዳም ምድር፥ በካሌብም ደቡብ ላይ ዘመትን፤ ጺቅላግንም በእሳት አቃጠልናት አለ። |
15. | ዳዊትም። ወደ እነዚያ ሠራዊት ዘንድ ልትመራኝ ትወድዳለህን? አለው፤ እርሱም። እንዳትገድለኝ፥ ለጌታዬም እጅ አሳልፈህ እንዳትሰጠኝ በአምላክ ማልልኝ እንጂ ወደ እነዚያ ሠራዊት እመራሃለሁ አለ። |
16. | ወደ ታችም እንዲወርድ ባደረገው ጊዜ፥ እነሆ፥ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ከብዙ ምርኮ ሁሉ የተነሣ በልተው ጠጥተውም የበዓልም ቀን አድርገው በምድር ሁሉ ላይ ተበትነው ነበር። |
17. | ዳዊትም ከማታ ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ማታ ድረስ መታቸው፤ ከእነርሱም በግመል ተቀምጠው ከሸሹ ከአራት መቶ ጕልማሶች በቀር አንድ ያመለጠ የለም። |
18. | ዳዊትም አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣላቸው፥ ሁለቱንም ሚስቶቹን አዳነ። |
19. | ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች፥ ከወሰዱትም ምርኮ ሁሉ፥ ታላቅም ሆነ ታናሽም ሆነ፥ ምንም የጐደለባቸው የለም፤ ዳዊትም ሁሉን አስጣለ። |
20. | ዳዊትም የበጉንና የላሙን መንጋ ሁሉ ወሰደ፥ ከራሱም ከብት ፊት እየነዳ። ይህ የዳዊት ምርኮ ነው አለ። |
21. | ዳዊትም ደክመው ዳዊትን ይከተሉት ዘንድ ወዳልቻሉ፥ በቦሦር ወንዝ ወዳስቀራቸው ወደ ሁለቱ መቶ ሰዎች መጣ፤ እነርሱም ዳዊትን ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሊቀበሉ ወጡ፤ ዳዊትም ወደ ሕዝቡ በቀረበ ጊዜ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። |
22. | ከዳዊትም ጋር ከሄዱ ሰዎች ክፉዎቹና ምናምንቴዎቹ ሁሉ። እነዚህ ከእኛ ጋር አልመጡምና እየራሳቸው ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ይሂዱ እንጂ ካስጣልነው ምርኮ ምንም አንሰጣቸውም አሉ። |
23. | ዳዊትም። ወንድሞቼ ሆይ፥ የጠበቀን በእኛም ላይ የመጣውን ጭፍራ በእጃችን አሳልፎ የሰጠን እግዚአብሔር በሰጠን ነገር እንዲህ አታድርጉ፤ |
24. | ይህንስ ነገ ማን ይሰማችኋል? ነገር ግን የተዋጉትና ዕቃውን የጠበቁት እድል ፈንታ እኩል ይሆናል፥ አንድነት ይካፈላሉ አለ። |
25. | ከዚያም ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ለእስራኤል ሥርዓትና ፍርድ አደረገው። |
26. | ዳዊትም ወደ ጺቅላግ በመጣ ጊዜ ለዘመዶቹ ለይሁዳ ሽማግሌዎች። እነሆ ከእግዚአብሔር ጠላቶች ምርኮ በረከትን ተቀበሉ ብሎ ከምርኮው ሰደደላቸው። |
27. | በቤቴል ለነበሩ፥ በራሞት በደቡብ ለነበሩ |
28. | በየቲር ለነበሩ፥ በአሮዔር ለነበሩ፥ በሢፍሞት ለነበሩ፥ በኤሽትሞዓ ለነበሩ፥ |
29. | በቀርሜሎስ ለነበሩ፥ በይረሕምኤላውያንና በቄናውያን ከተሞችም ለነበሩ፥ |
30. | በሔርማ ለነበሩ፥ በቦራሣን ለነበሩ፥ በዓታክ ለነበሩ፥ በኬብሮን ለነበሩ፥ |
31. | ዳዊትና ሰዎቹም በተመላለሱበት ስፍራ ለነበሩ ሰዎች ሁሉ ላከ። |
← 1Samuel (30/31) → |