| ← 1Samuel (24/31) → |
| 1. | እንዲህም ሆነ፤ ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ከተመለሰ በኋላ። እነሆ፥ ዳዊት በዓይንጋዲ ምድረ በዳ አለ የሚል ወሬ ደረሰለት። |
| 2. | ሳኦልም ከእስራኤል ሁሉ የተመረጡትን ሦስት ሺህ ሰዎች ወሰደ፥ ዳዊትንና ሰዎቹንም ለመፈለግ የበረሀ ፍየሎች ወደ ነበሩባቸው ዓለቶች ሄደ። |
| 3. | በመንገድም አጠገብ ወዳሉት የበጎች ማደሪያዎች መጣ፥ በዚያም ዋሻ ነበረ፤ ሳኦልም ወገቡን ይሞክር ዘንድ ከዚያ ገባ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከዋሻው በውስጠኛው ቦታ ተቀምጠው ነበር። |
| 4. | የዳዊትም ሰዎች። እነሆ፥ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ በዓይንህም ደስ የሚያሰኝህን ታደርግበታለህ ብሎ እግዚአብሔር የነገረህ ቀን፥ እነሆ፥ ዛሬ ነው አሉት። ዳዊትም ተነሥቶ የሳኦልን መጎናጸፊያ ዘርፍ በቀስታ ቈረጠ። |
| 5. | ከዚያም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የሳኦልን የልብሱን ዘርፍ ስለቈረጠ የዳዊት ልብ በኀዘን ተመታ። |
| 6. | ሰዎቹንም። እግዚአብሔር የቀባው ነውና እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ እጄንም እጥልበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው አላቸው። |
| 7. | ዳዊትም በዚህ ቃል ሰዎቹን ከለከላቸው፥ በሳኦልም ላይ ይነሡ ዘንድ አልተዋቸውም፤ ሳኦልም ከዋሻው ተነሥቶ መንገዱን ሄደ። |
| 8. | ከእርሱም በኋላ ዳዊት ደግሞ ተነሣ፥ ከዋሻውም ወጣ፥ ከሳኦልም በኋላ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ብሎ ጮኸ፤ ሳኦልም ወደ ኋላው ተመለከተ፥ ዳዊትም ወደ ምድር ተጐንብሶ እጅ ነሣ። |
| 9. | ዳዊትም ሳኦልን አለው። እነሆ፥ ዳዊት ክፉ ነገር ይሻብሃል የሚሉህን ሰዎች ቃል ለምን ትሰማለህ? |
| 10. | እነሆ፥ ዛሬ በዋሻው ውስጥ እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ እንደ ሰጠህ ዓይንህ አይታለች፤ አንተንም እንድገድልህ ሰዎች ተናገሩኝ፤ እኔ ግን። በእግዚአብሔር የተቀባ ነውና እጄን በጌታዬ ላይ አልዘረጋም ብዬ ራራሁልህ። |
| 11. | ደግሞም፥ አባቴ ሆይ፥ የልብስህ ዘርፍ በእጄ እንዳለ ተመልክተህ እወቅ፤ የልብስህንም ዘርፍ በቈረጥሁ ጊዜ አልገደልሁህም፤ ስለዚህም በእጄ ክፋትና በደል እንደሌለ፥ አንተም ነፍሴን ልትወስድ ምንም ብታሳድደኝ እንዳልበደልሁህ ተመልክተህ እወቅ። |
| 12. | እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፥ እግዚአብሔርም አንተን ይበቀልልኝ፤ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም። |
| 13. | በጥንት ምሳሌ። ከኃጢአተኞች ኀጢአት ይወጣል እንደ ተባለ፤ እጄ ግን በአንተ ላይ አትሆንም። |
| 14. | የእስራኤል ንጉሥ ማንን ለማሳደድ መጥቶአል? አንተስ ማንን ታሳድዳለህ? የሞተ ውሻን ወይስ ቁንጫን ታሳድዳለህን? |
| 15. | እንግዲህ እግዚአብሔር ዳኛ ይሁን፥ በእኔና በአንተም መካከል ይፍረድ፥ አይቶም ይምዋገትልኝ፥ ከእጅህም ያድነኝ። |
| 16. | እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ይህን ቃል ለሳኦል መናገር በፈጸመ ጊዜ፥ ሳኦል። ልጄ ሆይ ዳዊት፥ ይህ ድምፅህ ነውን? አለ፤ ሳኦልም ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ። |
| 17. | ዳዊትን አለው። እኔ ክፉ በመለስሁልህ ፋንታ በጎ መልሰህልኛልና አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ። |
| 18. | እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ አልገደልኸኝምና ለእኔ መልካም እንዳደረግህልኝ አንተ ዛሬ አሳየኸኝ። |
| 19. | ጠላቱን አግኝቶ በመልካም መንገድ ሸኝቶ የሚሰድድ ማን ነው? ስለዚህ ለእኔ ስላደረግኸው ቸርነት እግዚአብሔር ይመልስልህ። |
| 20. | አሁንም፥ እነሆ፥ አንተ በእርግጥ ንጉሥ እንድትሆን የእስራኤልም መንግሥት በእጅህ እንድትጸና እኔ አውቃለሁ። |
| 21. | አሁን እንግዲህ ከእኔ በኋላ ዘሬን እንዳትቈርጥ ከአባቴም ቤት ስሜን እንዳታጠፋው በእግዚአብሔር ማልልኝ። |
| 22. | ዳዊትም ለሳኦል ማለለት፤ ሳኦልም ወደ ቤቱ ሄደ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ አምባው ወጡ። |
| ← 1Samuel (24/31) → |