← 1Samuel (21/31) → |
1. | ዳዊትም ወደ ካህኑ ወደ አቢሜሌክ ወደ ኖብ መጣ፤ አቢሜሌክም እየተንቀጠቀጠ ዳዊትን ሊገናኘው መጣና። ስለ ምን አንተ ብቻህን ነህ? ከአንተስ ጋር ስለ ምን ማንም የለም? አለው። |
2. | ዳዊትም ካህኑን አቢሜሌክን። የተላክህበትን ነገርና የሰጠሁህን ትእዛዝ ማንም አይወቅ ብሎ ንጉሡ አንድ ነገር አዝዞኛል፤ ስለዚህም ብላቴኖቹን እንዲህ ባለ ስፍራ ተውኋቸው። |
3. | አሁንስ በእጅህ ምን አለ? አምስት እንጀራ ወይም የተገኘውን በእጄ ስጠኝ አለው። |
4. | ካህኑም ለዳዊት መልሶ። ሁሉ የሚበላው እንጀራ የለኝም፥ ነገር ግን የተቀደስ እንጀራ አለ፤ ብላቴኖቹ ከሴቶቹ ንጹሐን እንደ ሆኑ መብላት ይቻላል አለው። |
5. | ዳዊትም ለካህኑ መልሶ። በእውነት ከወጣን ጀምረን እኛ ሰውነታችንን ከሴቶች ሦስት ቀን ጠብቀናል፤ የብላቴኖችም ዕቃ የተቀደሰች ናት፤ ስለዚህ ዛሬ ዕቃቸው የተቀደሰች በመሆንዋ እንጀራው እንደሚበላ እንጀራ ይሆናል አለው። |
6. | ካህኑም በእርሱ ፋንታ ትኩስ እንጀራ ይደረግ ዘንድ ከእግዚአብሔር ፊት ከተነሣው ከገጹ ኅብስት በቀር ሌላ እንጀራ አልነበረምና የተቀደሰውን እንጀራ ሰጠው። |
7. | በዚያም ቀን ከሳኦል ባሪያዎች አንድ ሰው በዚያ በእግዚአብሔር ፊት ተገኝቶ ነበር፤ ስሙም ኤዶማዊው ዶይቅ ነበረ፥ ለሳኦልም የእረኞቹ አለቃ ነበረ። |
8. | ዳዊትም አቢሜሌክን። የንጉሥ ጉዳይ ስላስቸኰለኝ ሰይፌንና መሣሪያዬን አላመጣሁምና በአንተ ዘንድ ጦር ወይም ሰይፍ አለ ወይ? አለው። |
9. | ካህኑም። በኤላ ሸለቆ የገደልኸው የፍልስጥኤማዊው የጎልያድ ሰይፍ፥ እነሆ፥ በመጎናጸፊያ ተጠቅልሎ ከዚህ ከኤፉዱ በኋላ አለ፤ ትወድደውም እንደ ሆነ ውሰደው፤ ሌላ ከዚህ የለም አለ። ዳዊትም። እንደ እርሱ ያለ የለምና እርሱን ስጠኝ አለው። |
10. | ዳዊትም ተነሣ በዚያም ቀን ሳኦልን ፈርቶ ሸሸ፥ ወደ ጌትም ንጉሥ ወደ አንኩስ ሄደ። |
11. | የአንኩስ ባሪያዎችም። ይህ ዳዊት የአገሩ ንጉሥ አይደለምን? ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ ብለው ሴቶች በዘፈን የዘመሩለት እርሱ አይደለምን? አሉት። |
12. | ዳዊትም ይህን ቃል በልቡ አኖረ፥ የጌትንም ንጉሥ አንኩስን እጅግ ፈራ። |
13. | በፊታቸውም አእምሮውን ለወጠ፥ በያዙትም ጊዜ እንደ እብድ ሆነ፥ በበሩም መድረክ ላይ ተንፈራፈረ፥ ልጋጉም በጢሙ ላይ ይወርድ ነበር። |
14. | አንኩስም ባሪያዎቹን። እነሆ፥ ይህ ሰው እብድ እንደ ሆነ አይታችኋል፤ ለምን ወደ እኔ አመጣችሁት? በፊቴ ያብድ ዘንድ ይህን ያመጣችሁት እብድ ጠፍቶብኝ ነውን? እንዲህ ያለውስ ወደ ቤቴ ይገባልን? አላቸው። |
← 1Samuel (21/31) → |