1Samuel (18/31)  

1. ዳዊትም ለሳኦል መናገሩን በፈጸመ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፥ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው።
2. በዚያም ቀን ሳኦል ወሰደው፥ ወደ አባቱም ቤት ይመልሰው ዘንድ አልተወውም።
3. ዮናታንም እንደ ነፍሱ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።
4. ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ሸለመው። ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ቀስቱንም መታጠቂያውንም ለዳዊት ሸለመው።
5. ዳዊትም ሳኦል ወደ ሰደደው ሁሉ ይሄድ ነበር፥ አስተውሎም ያደርግ ነበር፤ ሳኦልም በጦረኞች ላይ ሾመው፤ ይህም በሕዝብ ሁሉ ዓይን እና በሳኦል ባሪያዎች ዓይን መልካም ነበረ።
6. እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና እየዘፈኑ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ።
7. ሴቶችም። ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር።
8. ሳኦልም እጅግ ተቈጣ፥ ይህም ነገር አስከፋው፤ እርሱም። ለዳዊት እልፍ ሰጡት፥ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፤ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት? አለ።
9. ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ ተመለከተው።
10. በነጋውም ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፥ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ።ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር።
11. ሳኦልም። ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ ብሎ ጦሩን ወረወረ። ዳዊትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ።
12. እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ዳዊትን ፈራው።
13. ስለዚህም ሳኦል ከእርሱ አራቀው፥ የሺህ አለቃም አደረገው፤ በሕዝቡም ፊት ይወጣና ይገባ ነበር።
14. ዳዊትም በአካሄዱ ሁሉ አስተውሎ ያደርግ ነበር፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።
15. ሳኦልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው።
16. ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለ ነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱ።
17. ሳኦልም ዳዊትን። ታላቂቱ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርስዋን እድርልሃለሁ፤ ብቻ ቀልጣፋ ልጅ ሁንልኝ፥ ስለ እግዚአብሔርም ጦርነት ተጋደል አለው። ሳኦልም። የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ትሁን እንጂ የእኔ እጅ በእርሱ ላይ አትሁን ይል ነበር።
18. ዳዊትም ሳኦልን። ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ ምንድር ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድር ነው? አለው።
19. ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤስድሪኤል ተዳረች።
20. የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደች፤ ይህም ወሬ ለሳኦል ደረሰለት፥ ነገሩም ደስ አሰኘው።
21. ሳኦልም። ወጥመድ ትሆነው ዘንድ፥ የፍልስጥኤማውያንም እጅ በእርሱ ላይ ትሆን ዘንድ እርስዋን እድርለታለሁ አለ፤ ሳኦልም ዳዊትን። ዛሬ ሁለተኛ አማች ትሆነኛለህ አለው።
22. ሳኦልም ባሪያዎቹን። እነሆ፥ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፥ ባሪያዎቹም ሁሉ ወድደውሃል፥ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን ብላችሁ በስውር ለዳዊት ንገሩት ብሎ አዘዛቸው።
23. የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል በዳዊት ጆሮ ተናገሩ፤ ዳዊትም። እኔ ድሀ የተጠቃሁም ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን? አለ።
24. የሳኦልም ባሪያዎች። ዳዊት እንዲህ ብሎ ተናገረ ብለው ነገሩት።
25. ሳኦልም ዳዊትን በፍልስጥኤማውያን እጅ ይጥለው ዘንድ አስቦ። የንጉሥን ጠላቶች ይበቀል ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት አላቸው።
26. የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል ለዳዊት ነገሩት፥ ለንጉሥም አማች ይሆን ዘንድ ዳዊትን ደስ አሰኘው።
27. ዳዊትና ሰዎቹም ተነሥተው ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም መቶ ሰዎች ገደሉ፤ ዳዊትም ለንጉሥ አማች ይሆን ዘንድ ሰለባቸውን አምጥቶ በቍጥራቸው ልክ ለንጉሡ ሰጠ። ሳኦልም ልጁን ሜልኮልን ዳረለት።
28. ሳኦልም እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነ አየ፤ እስራኤልም ሁሉ ወደዱት።
29. ሳኦልም ዳዊትን አጥብቆ ፈራው፤ ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ።
30. የፍልስጥኤማውያንም አለቆች ይወጡ ነበር፤ በወጡም ጊዜ ሁሉ ከሳኦል ባሪያዎች ሁሉ ይልቅ ዳዊት አስተውሎ ያደርግ ነበርና ስሙ እጅግ ተጠርቶ ነበር።

  1Samuel (18/31)