| ← 1Samuel (16/31) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሳሙኤልን። በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ፤ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ አለው። |
| 2. | ሳሙኤልም። እንዴት እሄዳለሁ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል አለ። እግዚአብሔርም። አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፥ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ በል። |
| 3. | እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፥ የምታደርገውንም አስታውቅሃለሁ፤ የምነግርህንም ቅባልኝ አለው። |
| 4. | ሳሙኤልም እግዚአብሔር የተናገረውን አደረገ፥ ወደ ቤተ ልሔምም መጣ። የአገሩም ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡና። የመጣኸው ለደኅንነት ነውን? አሉት። |
| 5. | እርሱም። ለደኅንነት ነው፤ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ፤ ቅዱሳን ሁኑ፥ ከእኔም ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ አለ። እሴይንና ልጆቹንም ቀደሳቸው፥ ወደ መሥዋዕቱም ጠራቸው። |
| 6. | እንዲህም ሆነ፤ በመጡ ጊዜ ወደ ኤልያብ ተመልክቶ። በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው አለ። |
| 7. | እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን። ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። |
| 8. | እሴይም አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት አሳለፈው፤ እርሱም። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ። |
| 9. | እሴይም ሣማን አሳለፈው፤ እርሱም። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ። |
| 10. | እሴይም ከልጆቹ ሰባቱን በሳሙኤል ፊት አሳለፋቸው። ሳሙኤልም እሴይን። እግዚአብሔር እነዚህን አልመረጠም አለው። |
| 11. | ሳሙኤልም እሴይን። የቀረ ሌላ ልጅ አለህን? አለው። እርሱም። ታናሹ ገና ቀርቶአል፤ እነሆም፥ በጎችን ይጠብቃል አለ። ሳሙኤልም እሴይን። እርሱ እስኪመጣ ድረስ አንረፍቅምና ልከህ አስመጣው አለው። |
| 12. | ልኮም አስመጣው፤ እርሱም ቀይ፥ ዓይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም። ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው አለ። |
| 13. | ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ። |
| 14. | የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው። |
| 15. | የሳኦልም ባሪያዎች። እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል፤ |
| 16. | በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጁ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት። |
| 17. | ሳኦልም ባሪያዎቹን። መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው። |
| 18. | ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ። እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፤ እርሱም ጽኑዕ ኃያል ነው፥ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ። |
| 19. | ሳኦልም ወደ እሴይ መልክተኞች ልኮ። ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ አለ። |
| 20. | እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ የፍየልም ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዋት እጅ ወደ ሳኦል ላከ። |
| 21. | ዳዊትም ወደ ሳኦል መጣ፥ በፊቱም ቆመ፤ እጅግም ወደደው፥ ለእርሱም ጋሻ ጃግሬው ሆነ። |
| 22. | ሳኦልም ወደ እሴይ። በዓይኔ ሞገስ አግኝቶአልና ዳዊት በፊቴ፥ እባክህ፥ ይቁም ብሎ ላከ። |
| 23. | እንዲህም ሆነ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤ ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር። |
| ← 1Samuel (16/31) → |