← 1Samuel (13/31) → |
1. | ሳኦልም በእስራኤል ላይ ሁለት ዓመት ከነገሠ በኋላ፥ |
2. | ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎች ከእስራኤል መረጠ፤ ሁለቱም ሺህ በማክማስና በቤቴል ተራራ ከሳኦል ጋር ነበሩ፥ አንዱም ሺህ በብንያም ጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ፤ የቀረውንም ሕዝብ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ አሰናበተ። |
3. | ዮናታንም በናሲብ ውስጥ የነበረውን የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መታ፥ ፍልስጥኤማውያንም ያን ሰሙ፤ ሳኦልም። ዕብራውያን ይስሙ ብሎ በአገሩ ሁሉ ቀንደ መለከት ነፋ። |
4. | እስራኤልም ሁሉ ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ እንደ መታ፥ ደግሞም እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ተጸየፉ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ። |
5. | ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ተሰበሰቡ፤ ሠላሳ ሺህ ሰረገሎች ስድስትም ሺህ ፈረሰኞች በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበሩ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በምሥራቅ በኩል በማክማስ ሰፈሩ። |
6. | ሕዝቡም ተጨንቀው ነበርና የእስራኤል ሰዎች በጭንቀት እንዳሉ ባዩ ጊዜ ሕዝቡ በዋሻና በእሾህ ቍጥቋጦ በገደልና በግንብ በጕድጓድም ውስጥ ተሸሸጉ። |
7. | ከዕብራውያንም ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ፤ ሳኦል ግን ገና በጌልገላ ነበረ፥ ሕዝቡም ሁሉ ተንቀጥቅጠው ተከተሉት። |
8. | ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ጊዜ ሰባት ቀን ቆየ፤ ሳሙኤል ግን ወደ ጌልገላ አልመጣም፥ ሕዝቡም ከእርሱ ተለይተው ተበታተኑ። |
9. | ሳኦልም። የሚቃጠል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት አምጡልኝ አለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ። |
10. | የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በፈጸመ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲመርቀው ሊገናኘው ወጣ። |
11. | ሳሙኤልም። ያደረግኸው ምንድር ነው? አለ። ሳኦልም። ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፥ አንተም በቀጠሮው እንዳልመጣህ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ማክማስ እንደ ተሰበሰቡ አየሁ፤ |
12. | ሰለዚህ። ፍልስጥኤማውያን አሁን ወደ ጌልገላ ይወርዱብኛል፥ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም አልሁ፤ ስለዚህም ሳልታገሥ የሚቃጠልን መሥዋዕት አሳረግሁ አለ። |
13. | ሳሙኤልም ሳኦልን። አላበጀህም፤ አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጽንቶልህ ነበረ። |
14. | አሁንም መንግሥትህ አይጸናም፤ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል፤ እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዞታል አለው። |
15. | ሳሙኤልም ከጌልገላ ተነሥቶ መንገዱን ሄደ፤ የቀሩትም ሕዝብ ሳኦልን ተከተለው ሰልፈኞቹን ሊገናኙ ሄዱ። ከጌልገላም ተነሥተው ወደ ብንያም ጊብዓ መጡ፤ ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፥ ስድስት መቶም የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ። |
16. | ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ከእነርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ በብንያም ጊብዓ ተቀመጡ፤ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ ሰፈሩ። |
17. | ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር ማራኪዎች በሦስት ክፍል ሆነው ወጡ፤ አንዱም ክፍል በዖፍራ መንገድ ወደ ሦጋል ምድር ሄደ። |
18. | ሁለተኛው ክፍል ወደ ቤት ሖሮን መንገድ ዞረ፤ ሦስተኛውም ክፍል በበረሃው አጠገብ ባለው ወደ ስቦይም ሸለቆ በሚመለከተው በዳርቻ መንገድ ዞረ። |
19. | ፍልስጥኤማውያንም። ዕብራውያን ሰይፍና ጦር እንዳይሠሩ ብለው ነበርና በእስራኤል ምድር ሁሉ ብረተ ሠሪ አልተገኘም። |
20. | እስራኤልም ሁሉ የማረሻውን ጫፍና ማጭዱን መጥረቢያውንና መቆፈሪያውን ይስል ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርድ ነበር። |
21. | ለማረሻው ጫፍና ለመቆፈሪያው ዋጋው የሰቅል ከ3 እጅ 2ቱ እጅ ነበረ። መጥረቢያውንም ለማሳል መውጊያውንም ለማበጀት ዋጋው የሰቅል ከ3 እጅ 1ዱ እጅ ነበረ። |
22. | ስለዚህም በሰልፍ ቀን ሰይፍና ጦር ከሳኦልና ከዮናታን ጋር በነበሩ ሕዝብ ሁሉ እጅ አልተገኘም፤ ብቻ በሳኦልና በልጁ በዮናታን ዘንድ ተገኘ። የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ ወደ ማክማስ መተላለፊያ ወጡ። |
← 1Samuel (13/31) → |