← 1Samuel (12/31) → |
1. | ሳሙኤልም እስራኤልን ሁሉ አለ። የነገራችሁኝን ሁሉ ሰምቼ አንግሼላችኋለሁ። |
2. | አሁንም፥ እነሆ፥ ንጉሡ በፊታችሁ ይሄዳል፤ እኔም አርጅቻለሁ ሸምግያለሁም፤ እነሆም፥ ልጆቼ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በፊታችሁ ሄድሁ። |
3. | እነሆኝ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን ጋር እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? እኔም እመልስላችኋለሁ። |
4. | እነርሱም። አልሸነገልኸንም፥ ግፍም አላደረግህብንም፥ ከሰውም እጅ ምንም አልወሰድህም አሉ። |
5. | እርሱም። በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ እግዚአብሔርና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው አላቸው፤ እነርሱም። ምስክር ነው አሉ። |
6. | ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ። ሙሴንና አሮንን ያላቀ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ ምድር ያወጣ እግዚአብሔር ነው። |
7. | አሁንም እግዚአብሔር ለእናንተና ለአባቶቻችሁ ስላደረገው ጽድቅ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እምዋገታችሁ ዘንድ በዚህ ቁሙ። |
8. | ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ በገቡ ጊዜ ግብጻውያን አስጨነቁአቸው፤ አባቶቻችሁም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ላከ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ አውጥተው በዚህ ቦታ አኖሩአቸው። |
9. | አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ፥ ለአሶር ሠራዊትም አለቃ ለሲሣራ እጅ፥ ለፍልስጥኤማውያንም እጅ፥ ለሞዓብም ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጉ። |
10. | እነርሱም። እግዚአብሔርን ትተን በኣሊምንና አስታሮትን በማምለካችን በድለናል፤ አሁንም ከጠላቶቻችን እጅ አድነን፥ እናመልክህማለን ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። |
11. | እግዚአብሔርም ይሩበአልም፥ ባርቅንም፥ ዮፍታሔንም፥ ሳሙኤልንም ላከ፥ በዙሪያችሁም ካሉት ከጠላቶቻችሁ እጅ አዳናችሁ፤ ተዘልላችሁም ተቀመጣችሁ። |
12. | የአሞንም ልጆች ንጉሥ ናዖስ እንደ መጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ንጉሣችሁ ሳለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይንገሥልን አላችሁኝ። |
13. | አሁንም የመረጣችሁትንና የፈለጋችሁትን ንጉሥ እዩ፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ንጉሥ አደረገላችሁ። |
14. | እግዚአብሔርን ብትፈሩ ብታመልኩትም፥ ቃሉንም ብትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ባታምፁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ፥ መልካም ይሆንላችኋል። |
15. | ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ብታምፁ፥ በእናንተና በንጉሣችሁ ላይ የእግዚአብሔር እጅ ትሆናለች። |
16. | አሁንም ቁሙ፥ እግዚአብሔርም በዓይናችሁ ፊት ወደሚያደርገው ወደዚህ ታላቅ ነገር ተመልከቱ። |
17. | የስንዴ መከር ዛሬ አይደለምን? ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፥ እርሱም ነጎድጓድና ዝናብ ይልካል፤ እናንተም ንጉሥ በመለመናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ያደረጋችሁት ክፋት ታላቅ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ ታያላችሁም። |
18. | ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም በዚያን ቀን ነጐድጓድና ዝናብ ላከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩአቸው። |
19. | ሕዝቡም ሁሉ ሳሙኤልን። ንጉሥ በመለመናችን በኃጢአታችን ሁሉ ላይ ይህን ክፋት ጨምረናልና እንዳንሞት ስለ ባሪያዎችህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት። |
20. | ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ። አትፍሩ፤ በእውነት ይህን ክፋት ሁሉ አደረጋችሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ። |
21. | ምናምንቴ ነውና የማይረባንና የማያድን ከንቱን ነገር ለመከተል ፈቀቅ አትበሉ። |
22. | እግዚአብሔር ለእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ወድዶአልና እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም። |
23. | ደግሞ መልካሙንና ቅኑን መንገድ አስተምራችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይን በመተው እግዚአብሔርን እበድል ዘንድ ይህ ከእኔ ይራቅ። |
24. | ብቻ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ያደረገላችሁንም ታላቅ ነገር አይታችኋልና በፍጹም ልባችሁ በእውነት አምልኩት። |
25. | ነገር ግን ክፉ ብትሠሩ እናንተም ንጉሣችሁም ትጠፋላችሁ። |
← 1Samuel (12/31) → |