← 1Kings (9/22) → |
1. | ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ |
2. | እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። |
3. | እግዚአብሔርም አለው። በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። |
4. | ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንም ፍርዴንም ብትጠብቅ፥ |
5. | እኔ። ከእስራኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ። |
6. | እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከትል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዓቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ |
7. | እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ። |
8. | ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውም ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለምን እንዲህ አደረገ? ብሎ ይደነቃል። |
9. | መልሰውም። ከግብጽ ምድር አባቶቻቸውን ያወጣውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችንም አማልክት ስለ ተከተሉ፥ ስለ ሰገዱላቸውም፥ ስለ አመለኩአቸውም፥ ስለዚህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣባቸው ይላሉ። |
10. | ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት ሁለቱን ቤቶች የሠራበት ሀያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ |
11. | ንጉሡ ሰሎሞን በገሊላ ምድር ያሉትን ሀያ ከተሞች ለኪራም ሰጠው። የጢሮስም ንጉሥ ኪራም የሚሻውን ያህል የዝግባና የጥድ እንጨት የሚሻውንም ያህል ወርቅ ሁሉ ለሰሎሞን ሰጥቶት ነበር። |
12. | ኪራምም ሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ያይ ዘንድ ከጢሮስ ወጣ፤ ደስም አላሰኙትም። |
13. | እርሱም። ወንድሜ ሆይ፥ የሰጠኸኝ እነዚህ ከተሞች ምንድር ናቸው? አለ። እስከ ዛሬም ድረስ የከቡል አገር ተብለው ተጠሩ። |
14. | ኪራምም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ ለንጉሡ ላከ። |
15. | ንጉሡም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት፥ ሚሎንም፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር፥ ሐጾርንም፥ መጊዶንም፥ ጌዝርንም ይሠራ ዘንድ ገባሮችን መልምሎ ነበር። |
16. | የግብጽም ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ ጌዝርን ይዞ ነበር፥ በእሳትም አቃጥሎ ነበር፥ በከተማም የኖሩትን ከነዓናውያን ገድሎ ነበር፤ ለልጁም ለሰሎምን ሚስት ትሎት አድርጎ ሰጥቶአት ነበር። |
17. | ሰሎሞንም ጌዝርን፥ የታችኛውንም ቤት |
18. | ሖሮን፥ ባዕላትንም፥ በምድረ በዳም አገር ያለችውን ተድሞርን፥ |
19. | ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፥ የሰረገላውንም ከተሞች፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ። |
20. | ከእስራኤልም ልጆች ዘንድ ያልነበሩትን ከአሞራውያንና ከኬጢያውያን፥ ከፌርዛውያን፥ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን የቀሩትን፥ |
21. | የእስራኤልም ልጆች ያጠፉአቸው ዘንድ ያልቻሉትን፥ በኋላቸው የቀሩትን ልጆቻቸውን፥ ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው። |
22. | ሰሎሞንም ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ሰልፈኞች፥ ሎሌዎችም፥ መሳፍንትም፥ አለቆችም፥ የሰረገሎችና የፈረሶች ባልደራሶች ነበሩ። |
23. | ሰሎሞንም በሚሠራው ሥራ ላይ ሠራተኛውን ሕዝብ የሚያዝዙ አለቆች አምስት መቶ አምሳ ነበሩ። |
24. | የፈርዖንም ልጅ ከዳዊት ከተማ ሰሎሞን ወደ ሠራላት ወደ ቤትዋ ወጣች በዚያን ጊዜም ሚሎን ሠራ። |
25. | ሰሎሞንም በየዓመቱ ሦስት ጊዜ የሚቃጠለውንና የደኅንነቱን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በሠራው መሠዊያ ላይ ያሳርግ ነበር፤ በእግዚአብሔር ፊት ባለው መሠዊያ ላይ ዕጣን ያሳርግ ነበር፤ ቤቱንም ጨረሰ። |
26. | ንጉሡም ሰሎሞን በኤዶምያስ ምድር በኤርትራ ባሕር ዳር በኤሎት አጠገብ ባለችው በዔጽዮንጋብር መርከቦችን ሠራ። |
27. | ኪራምም በእነዚያ መርከቦች ከሰሎሞን ባሪያዎች ጋር የባሕሩን ነገር የሚያውቁ መርከበኞች ባሪያዎቹን ሰደደ። |
28. | ወደ ኦፊርም መጡ፥ ከዚያም አራት መቶ ሀያ መክሊተ ወርቅ ወሰዱ፥ ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን ይዘው መጡ። |
← 1Kings (9/22) → |