| ← 1Kings (6/22) → |
| 1. | የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ ዓመት በሆነ ጊዜ፥ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ በሚባለው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ። |
| 2. | ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር የሠራው ቤት ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ። |
| 3. | በመቅደሱም ፊት ወለል ነበረ፤ ርዝመቱም እንደ መቅደሱ ወርድ ሀያ ክንድ፥ ወርዱም ከቤቱ ወደፊት አሥር ክንድ ነበረ። |
| 4. | ለቤቱም በዓይነ ርግብ የተዘጉ መስኮቶች አደረገ። |
| 5. | በቤቱም ግንብ ዙሪያ፥ በመቅደሱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግንብ ዙሪያ፥ ደርብ ሠራ፥ በዙሪያውም ጓዳዎች አደረገ። |
| 6. | የታችኛውም ደርብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ የመካከለኛው ደርብ ወርዱ ስድስት ክንድ፥ የሦስተኛውም ደርብ ወርዱ ሰባት ክንድ ነበረ። ሰረገሎቹ በቤቱ ግንብ ውስጥ እንዳይገቡ ከቤቱ ግንብ ውጭ ዓረፍቶች አደረገ። |
| 7. | ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ፤ በተሠራም ጊዜ መራጃና መጥረቢያ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም። |
| 8. | የታችኛውም ደርብ ጓዳዎች በር በቤቱ ቀኝ አጠገብ ነበረ። ከዚያም ወደ መካከለኛው ደርብ፥ ከመካከለኛውም ወደ ሦስተኛው ደርብ በመውጫ ያስወጣ ነበር። |
| 9. | ቤቱንም ሠርቶ ፈጸመው፤ በዝግባው ሰረገሎችና ሳንቃዎች ከደነው። |
| 10. | በቤቱም ሁሉ ዙሪያ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆነ ደርቦች ሠራ፤ ከቤቱም ጋር በዝግባ እንጨት አጋጠማቸው። |
| 11. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን መጣ እንዲህ ሲል። |
| 12. | ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት በሥርዓቴ ብትሄድ፥ ፍርዴንም ብታደርግ፥ ትመላለስበትም ዘንድ ትእዛዜን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ። |
| 13. | በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ ሕዝቤንም እስራኤልን አልጥልም። |
| 14. | ሰሎሞንም ቤቱን ሠራው፥ ፈጸመውም። |
| 15. | የቤቱንም ግንብ ውስጡን በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ ከቤቱም መሠረት ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ ውስጡን በእንጨት ለበጠው፤ ደግሞም የቤቱን ወለል በጥድ እንጨት ከደነው። |
| 16. | በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን ይሆን ዘንድ ኋለኛውን ሀያውን ክንድ በዝግባ እንጨት ጋረደው። |
| 17. | በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ያለውም መቅደስ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበረ። |
| 18. | የቤቱንም ውስጥ በተጐበጐበና በፈነዳ አበባ በተቀረጸ ዝግባ ለበጠው፤ ሁሉም ዝግባ ነበረ፤ ድንጋዩም አልታየም ነበር። |
| 19. | በዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ያኖር ዘንድ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን አበጀ። |
| 20. | የቅድስተ ቅዱሳንም ርዝመት ሀያ ክንድ፥ ስፋቱም ሀያ ክንድ፥ ቁመቱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። |
| 21. | በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ከዝግባ የተሠራ መሠዊያ አደረገ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። |
| 22. | ቤቱንም ሁሉ ፈጽሞ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት የነበረውን መሠዊያ ሁሉ በወርቅ ለበጠው። |
| 23. | በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል ሠራ። |
| 24. | የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፥ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስክ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ አሥር ክንድ ነበረ። |
| 25. | ሁለተኛውም ኪሩብ አሥር ክንድ ነበረ፤ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበረ። |
| 26. | የአንዱ ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ። |
| 27. | ኪሩቤልንም በውስጠኛው ቤት አኖራቸው፤ የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር፥ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። |
| 28. | ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው። |
| 29. | በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸ። |
| 30. | የቤቱንም ወለል በውስጥና በውጭ በወርቅ ለበጠ። |
| 31. | ለቅዱስተ ቅዱሳኑም መግቢያ ከወይራ እንጨት ደጆች ሠራ፤ መድረኩንና መቃኖቹን ደፉንም አምስት ማዕዘን አደረገ። |
| 32. | ሁለቱንም ደጆች ከወይራ እንጨት ሠራ፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፥ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልናና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጣቸው። |
| 33. | እንዲሁም ለመቅደሱ መግቢያ ከወይራ እንጨት አራት ማዕዘን መቃን አደረገ። |
| 34. | ሁለቱንም ደጆች ከጥድ እንጨት ሠራ፤ አንዱ ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፥ ሁለተኛውም ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ። |
| 35. | የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፤ በተቀረጸውም ሥራ ላይ በወርቅ ለበጣቸው። |
| 36. | የውስጠኛውንም አደባባይ ቅጥር ሦስቱን ተራ በተጠረበ ድንጋይ፥ አንዱንም ተራ በዝግባ ሳንቃ ሠራው። |
| 37. | በአራተኛው ዓመት ዚፍ በሚባል ወር የእግዚአብሔር ቤት ተመሠረተ። |
| 38. | በአሥራ አንደኛውም ዓመት ቡል በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱ እንደ ክፍሎቹና እንደ ሥርዓቱ ሁሉ ተጨረሰ። በሰባትም ዓመት ውስጥ ሠራው። a |
| ← 1Kings (6/22) → |