1Kings (4/22)  

1. ንጉሡም ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር።
2. የነበሩትም አለቆች እነዚህ ናቸው፤ የሳዶቅ ልጅ ካህኑ ዓዛርያስ፥
3. ጸሐፊዎቹም የሴባ ልጆች ኤልያፍና አኪያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ፥
4. የዮዳሄም ልጅ በናያስ የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፤
5. የናታንም ልጅ ዓዛርያስ የሹሞች አለቃ ነበረ፤ የናታንም ልጅ ዛቡድ የንጉሡ አማካሪና ወዳጅ ነበረ፤
6. አሒሳርም የቤት አዛዥ፥ የዓብዳም ልጅ አዶኒራም አስገባሪ ነበረ።
7. ለንጉሡና ለቤተ ሰቡም ቀለብ የሚሰጡ በእስራኤል ሁሉ ላይ አሥራ ሁለት ሹሞች ለሰሎሞን ነበሩት። ከዓመቱ ውስጥ አንዱን ወር እያንዳንዳቸው ይቀልቡ ነበር።
8. ስማቸውም ይህ ነበረ፤ በተራራማው አገር በኤፍሬም የሑር ልጅ፤
9. በማቃጽና በሸዓልቢም በቤትሳሚስና በኤሎንቤትሐናን የዴቀር ልጅ፤
10. በአሩቦት የሔሴድ ልጅ፥ ለእርሱም ሰኰትና የኦፌር አገር ሁሉ ነበረ፤
11. በዶር አገር ዳርቻ ሁሉ የአሚናዳብ ልጅ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ጣፈትን አግብቶ ነበር፤
12. ከቤትሳን ጀምሮ እስከ አቤልምሖላና እስከ ዮቅምዓም ማዶ ድረስ በታዕናክና በመጊዶ በጸርታንም አጠገብ በኢይዝራኤል በታች ባለው በቤትሳን ሁሉ የአሒሉድ ልጅ በዓና ነበረ፤
13. በሬማት ዘገለዓድ የጌበር ልጅ ነበረ፥ ለእርሱም በገለዓድ ያሉት የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች ነበሩ፤ ለእርሱም ደግሞ በባሳን በአርጎብ ዳርቻ ያሉት ቅጥርና የናስ መወረወሪያዎች የነበረባቸው ስድሳ ታላላቅ ከተሞች ነበሩበት፤
14. በመሃናይም የዒዶ ልጅ አሒናዳብ፤
15. በንፍታሌም አኪማአስ ነበረ፥ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ባስማትን አግብቶ ነበር፤
16. በአሴርና በበዓሎት የኩሲ ልጅ በዓና፤
17. በይሳኮር የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ፤
18. በብንያም የኤላ ልጅ ሳሚ፤
19. በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎንና በባሳን ንጉሥ በዐግ አገር፥ በገለዓድ አገር፥ የኡሪ ልጅ ጌበር ነበረ፤ በዚያችም ምድር ላይ እርሱ ብቻውን ሹም ነበረ።
20. ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር።
21. ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ግብጽ ዳርቻ እስከ ፍልስጥኤም ድረስ በመንግሥታት ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር፤ ግብርም ያመጡለት ነበር፥ በዕድሜውም ሙሉ ለሰሎሞን ይገዙ ነበር።
22. ለሰሎሞንም ለቀን ለቀኑ ቀለብ የሚሆን ሠላሳ ኮር መልካም ዱቄትና ስድሳ ኮር መናኛ ድቄት፥
23. ከዋላና ከሚዳቋ ከበረሀ ፍየልና ከሰቡ ወፎች በቀር አሥር ፍሪዳዎች ሀያም የተሰማሩ በሬዎች አንድ መቶም በጎች ነበረ።
24. ከወንዙ ወዲህ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ከወንዙም ወዲህ ባለው አገር ሁሉ ላይ ከቲፍሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ ነግሦ ነበር፤ በዙሪያውም ባለው በሁሉ ወገን ሰላም ሆኖለት ነበር።
25. በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።
26. ለሰሎሞንም በአርባ ሺህ ጋጥ የሚገቡ የሰረገላ ፈረሶች አሥራ ሁለትም ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት።
27. እነዚያም ሹሞች እያንዳንዱ በየወሩ ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ማዕድ የሚቀርቡትን ሁሉ ይቀልቡ ነበር፤ ምንም አያጎድሉም ነበር።
28. እያንዳንዱም እንደ ደንቡ ለፈረሶቹና ለሰጋር በቅሎች ገብስና ጭድ ወደ ስፍራቸው ያመጡ ነበር።
29. እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው።
30. የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ።
31. ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ።
32. እርሱም ሦስት ሺህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሺህ አምስት ነበረ።
33. ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ሰለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር።
34. ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር። a

  1Kings (4/22)