← 1Kings (22/22) |
1. | ሶርያና እስራኤልም ሳይዋጉ ሦስት ዓመት ተቀመጡ። |
2. | በሦስተኛውም ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ። |
3. | የእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎቹን። ሬማት ዘገለዓድ የእኛ እንደ ሆነች፥ እኛም ከሶርያ ንጉሥ እጅ ሳንወስዳት ዝም እንዳልን ታውቃላችሁን? አላቸው። |
4. | ኢዮሣፍጥንም። በሬማት ዘገለዓድ እንዋጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ትመጣለህን? አለው። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው አለው። |
5. | ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው። |
6. | የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቶቹን አራት መቶ የሚያህሉትን ሰዎች ሰብስቦ። ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር? አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ አሉት። |
7. | ኢዮሣፍጥ ግን። እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን? አለ። |
8. | የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የይምላ ልጅ ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ አለው። ኢዮሣፍጥም። ንጉሥ እንዲህ አይበል አለ። |
9. | የእስራኤልም ንጉሥ አንዱን ጃንደረባ ጠርቶ። የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣ አለው። |
10. | የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቶቹም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። |
11. | የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ሶርያውያንን ትወጋለህ አለ። |
12. | ነቢያትም ሁሉ። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን እያሉ እንዲህ ትንቢት ይናገሩ ነበር። |
13. | ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ። እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ አለው። |
14. | ሚክያስም። ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ አለ። |
15. | ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ። ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር? አለው፤ እርሱም። ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል ብሎ መለሰለት። |
16. | ንጉሡም። ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ? አለው። |
17. | እርሱም። እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም። ለእነዚህ ጌታ የላቸውም እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ ብሎ ተናገረ። |
18. | የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁህምን? አለው። |
19. | ሚክያስም አለ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። |
20. | እግዚአብሔርም። ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው? አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ የለ ነገር ተናገረ። |
21. | መንፈስም ወጣ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ። እኔ አሳስተዋለሁ አለ። |
22. | እግዚአብሔርም። በምን? አለው፤ እርሱም። ወጥቼ በነቢያቶቹ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፥ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፥ እንዲሁም አድርግ አለ። |
23. | አሁንም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል። |
24. | የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና። አንተን ሊናገር የእግዚአብሔር መንፈስ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ? አለ። |
25. | ሚክያስም። እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ አለ። |
26. | የእስራኤልም ንጉሥ። ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም ሹም ወደ አሞን ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ። ንጉሡ እንዲህ ይላል። |
27. | በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉ አለ። |
28. | ሚክያስም። በደኅና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም አለ። ደግሞም። አሕዛብ ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ አለ። |
29. | የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። |
30. | የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ወደ ሰልፍ ገባ። |
31. | የሶርያም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሰረገሎች አለቆች። ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፥ ታናሽ ቢሆን ወይም ታላቅ ከማናቸውም ጋር አትግጠሙ ብሎ አዝዞ ነበር። |
32. | የሰረገሎች አለቆችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ። በእውነት የእስራኤል ንጉሥ ነው አሉ፤ ይገጥሙትም ዘንድ ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ። |
33. | የሰረገሎች አለቆችም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። |
34. | አንድ ሰውም ቀስቱን ድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ ልብስ መጋጠሚያ በኩል ወጋው፤ ሰረገለኛውንም። መልሰህ ንዳ፥ ተወግቻለሁና ከሰልፍ ውስጥ አውጣኝ አለው። |
35. | በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ ንጉሡም በሶርያውያን ፊት በሰረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፥ ማታም ሞተ፤ የቍስሉም ደም በሰረገላው ውስጥ ፈሰሰ። |
36. | በሠራዊቱም መካከል ፀሐይ ስትገባ። ንጉሡ ሞቶአልና እያንዳንዱ ወደ ከተማው፥ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሂድ የሚል ጩኸት ሆነ። |
37. | ወደ ሰማርያም መጡ፥ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት። |
38. | አመንዝሮች በታጠቡባት በሰማርያ ኵሬ ሰረገላውን አጠቡት፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ውሾች ደሙን ላሱት። |
39. | የቀረውም የአክዓብ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የሠራው ቤት፥ የሠራቸውም ከተሞች ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? |
40. | አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በእርሱም ፋንታ ልጁ አካዝያስ ነገሠ። |
41. | አክዓብም በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ። |
42. | ኢዮሣፍጥ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ አምስት ዓመት ጎበዝ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሀያ አምስት ዓመት ነገሠ። እናቱም ዓዙባ የተባለች የሺልሒ ልጅ ነበረች። |
43. | በአባቱም በአሳ መንገድ ሁሉ ሄደ፥ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን አደረገ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ ሕዝቡ ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። |
44. | ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ታረቀ። vፕ |
45. | የቀረውም የኢዮሣፍጥ ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ እንዴትም እንደ ተወጋ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? |
46. | ከአባቱ ከአሳ ዘመን የተረፉትን ሰዶማውያን ከምድር አጠፋ። |
47. | በኤዶምያስም ንጉሥ አልነበረም፤ ሹሙም እንደ ንጉሥ ነበረ። |
48. | ኢዮሣፍጥም ወደ ኦፊር ሄደው ወርቅ ያመጡ ዘንድ የተርሴስን መርከቦች ሠራ፤ ነገር ግን መርከቦቹ በዔጽዮንጋብር ተሰበሩ እንጂ አልሄዱም። |
49. | የአክዓብም ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን። ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋር በመርከብ ይሂዱ አለው፤ ኢዮሣፍጥ ግን አልወደደም። |
50. | ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። |
51. | በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በአሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። |
52. | በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፥ በአባቱና በእናቱም መንገድ፥ እስራኤልንም ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሄደ። |
53. | በኣልንም አመለከ ሰገደለትም፤ አባቱም እንዳደረገ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ። |
← 1Kings (22/22) |