1Kings (20/22)  

1. ለኢይዝራኤላዊውም ለናቡቴ በሰማርያ ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን ቦታ ነበረው።
2. አክዓብም ናቡቴን። በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ቦታ አደርገው ዘንድ የወይን ቦታህን ስጠኝ፤ ስለ እርሱም ከእርሱ የተሻለ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ወይም ብትወድድ ግምቱን ገንዘብ እሰጥሃለሁ ብሎ ተናገረው።
3. ናቡቴም አክዓብን። የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ አለው።
4. ኢይዝራኤላዊውም ናቡቴ። የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም ብሎ ስለ ተናገረው አክዓብ ተቈጥቶና ተናድዶ ወደ ቤቱ ገባ። በአልጋውም ላይ ተጋድሞ ፊቱን ተሸፋፈነ፥ እንጀራም አልበላም።
5. ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ መጥታ። ልብህ የሚያዝን እንጀራስ የማትበላ ስለምንድር ነው? አለችው።
6. እርሱም። ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን። የወይንህን ቦታ በገንዘብ ስጠኝ፤ ወይም ብትወድድ በፋንታው ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ ብዬ ተናገርሁት፤ እርሱ ግን። የወይን ቦታዬን አልሰጥህም ብሎ ስለ መለሰልኝ ነው አላት።
7. ሚስቱም ኤልዛቤል። አንተ አሁን የእስራኤልን መንግሥት ትገዛለህን? ተነሣ እንጀራም ብላ፥ ልብህም ደስ ይበላት፤ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ አለችው።
8. በአክዓብም ስም ደብዳቤ ጻፈች፥ በማኅተሙም አተመችው፤ በከተማው ወደ ነበሩትና ከናቡቴም ጋር ወደ ተቀመጡት ሽማግሌዎችና ከበርቴዎች ደብዳቤውን ላከች።
9. በደብዳቤውም። ስለ ጾም አዋጅ ንገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀምጡት፤
10. ሁለትም ምናምንቴ ሰዎች በፊቱ አስቀምጡና። እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው ይመስክሩበት፤ አውጥታችሁም እስኪሞት ድረስ ውገሩት ብላ ጻፈች።
11. በከተማውም የተቀመጡት የከተማው ሰዎችና ሽማግሌዎች ከበርቴዎችም ኤልዛቤል እንዳዘዘቻቸውና ወደ እነርሱ በተላከው ደብዳቤ እንደ ተጻፈ እንዲሁ አደረጉ።
12. የጾም አዋጅ ነገሩ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀመጡት።
13. ሁለቱም ምናምንቴ ሰዎች ገብተው በፊቱ ተቀመጡ፤ ምናምንቴዎቹ ሰዎችም በሕዝቡ ፊት። ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል ብለው በናቡቴ ላይ መሰከሩ። የዚያን ጊዜም ከከተማ አውጥተው እስኪሞት ድረስ ወገሩት።
14. ወደ ኤልዛቤልም። ናቡቴ ተወግሮ ሞተ ብለው ላኩ።
15. ኤልዛቤልም ናቡቴ ተወግሮ እንደ ሞተ በሰማች ጊዜ ኤልዛቤል አክዓብን። ናቡቴ ሞቶአል እንጂ በሕይወት አይደለምና በገንዘብ ይሰጥህ ዘንድ እንቢ ያለውን የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ ተነሥተህ ውረስ አለችው።
16. አክዓብም ናቡቴ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ ይወርሰው ዘንድ ወደ ኢይዝራኤላዊው ወደ ናቡቴ ወይን ቦታ ሊወርድ ተነሣ።
17. የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ።
18. ተነሥተህ በሰማርያ የሚኖረውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ እነሆ፥ ይወርሰው ዘንድ በወረደበት በናቡቴ የወይን ቦታ ውስጥ አለ።
19. አንተም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ገድለህ ወረስኸውን? ብለህ ንገረው። ደግሞም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል ብለህ ንገረው።
20. አክዓብም ኤልያስን። ጠላቴ ሆይ፥ አገኘኸኝን? አለው። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት። አግኝቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ለማድረግ ራስህን ሽጠሃልና።
21. እነሆ፥ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፥ ፈጽሞም እጠርግሃለሁ፥ ከአክዓብም በእስራኤል ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ አጠፋለሁ፤
22. በሥራህም አስቈጥተኸኛልና፥ እስራኤልንም አስተሃልና ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።
23. ደግሞ እግዚአብሔር ስለ ኤልዛቤል። በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ኤልዛቤልን ውሾች ይበሉአታል ብሎ ተናገረ።
24. ከአክዓብም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።
25. በእግዚአብሔር ፊት ክፋት ለመሥራት ራሱን እንደ ሸጠ፥ ሚስቱም ኤልዛቤል እንደ ነዳችው፥ እንደ አክዓብ ያለ ሰው አልነበረም።
26. እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ያጠፋቸው አሞራውያን እንደ ሠሩት ሁሉ፥ ጣዖታትን በመከተል እጅግ ርኩስ ነገር ሠራ።
27. አክዓብም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ ገላውን ማቅ አለበሰ፥ ጾመም፥ በማቅ ላይም ተኛ፥ ቅስስ ብሎም ሄደ።
28. ደግሞም። አክዓብ በፊቴ እንደ ተዋረደ አየህን? በፊቴ የተዋረደ ስለ ሆነ በልጁ ዘመን በቤቱ ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ እንጂ በእርሱ ዘመን ክፉ ነገር አላመጣም የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ መጣ።

  1Kings (20/22)