1Kings (18/22)  

1. ከብዙ ቀንም በኋላ በሦስተኛው ዓመት። ሂድ፥ ለአክዓብ ተገለጥ፥ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ።
2. ኤልያስም ለአክዓብ ይገለጥ ዘንድ ሄደ፤ በሰማርያም ራብ ጸንቶ ነበር።
3. አክዓብም የቤቱን አዛዥ አብድዩን ጠራ፤ አብድዩ እግዚአብሔርን እጅግ ይፈራ ነበር።
4. ኤልዛቤልም የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ እርሱ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውኃ ይመግባቸው ነበር።
5. አክዓብም አብድዩን። በአገሩ መካከል ወደ ውኃው ምንጭ ሁሉና ወደ ወንዝ ሁሉ ሂድ፤ እንስሶችም ሁሉ እንዳይጠፉ ፈረሶችንና በቅሎችን የምናድንበት ሣር ምናልባት እናገኛለን አለው።
6. ሁለቱም የሚመለሱበትን አገር ተካፈሉ፤ አክዓብም ለብቻው በአንድ መንገድ አብድዩም ለብቻው በሌላ መንገድ ሄዱ።
7. አብድዩም በመንገድ ሲሄድ፥ እነሆ፥ ኤልያስ ተገናኘው፤ አብድዩም አወቀው፥ በግምባሩም ተደፍቶ። ጌታዬ ሆይ፥ ኤልያስ አንተ ነህን? አለ።
8. ኤልያስም። እኔ ነኝ ሄደህ ለጌታህ። ኤልያስ ተገኝቶአል በል አለው።
9. አብድዩም አለ። እኔን ባሪያህን እንዲገድል በአክዓብ እጅ አሳልፈህ ትሰጠኝ ዘንድ ምን ኃጢአት አድርጌአለሁ?
10. አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! ጌታዬ ይፈልግህ ዘንድ ያልላከበት ሕዝብ ወይም መንግሥት የለም፤ ሁሉም። በዚህ የለም ባሉ ጊዜ አንተን እንዳላገኙ መንግሥቱንና ሕዝቡን አምሎአቸው ነበር።
11. አሁንም፥ እነሆ። ሂድ፥ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር ትለኛለህ።
12. እኔም ከአንተ ጥቂት ራቅ ስል የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወደማላውቀው ስፍራ ይወስድሃል፤ እኔም ገብቼ ለአክዓብ ስናገር፥ ባያገኝህ ይገድለኛል፤ እኔም ባሪያህ ከትንሽነቴ ጀምሬ እግዚአብሔርን እፈራ ነበር።
13. ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ፥ መቶውን የእግዚአብሔር ነቢያት ወስጄ፥ አምሳ አምሳውንም በዋሻ ውስጥ ሸሽጌ፥ እንጀራና ውኃ የመገብኋቸው፥ ይህ ያደርግሁት ነገር በውኑ ለጌታዬ አልታወቀህምን?
14. አሁንም። ሄደህ ኤልያስ ተገኘ ብለህ ለጌታህ ንገር ትላለህ፤ እርሱም ይገድለኛል።
15. ኤልያስም። በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ ዛሬ ለእርሱ እገለጣለሁ አለ።
16. አብድዩም አክዓብን ሊገናኘው ሄደ፥ ነገረውም፤ አክዓብም ኤልያስን ሊገናኘው መጣ።
17. አክዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ። እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን? አለው።
18. ኤልያስም። እስራኤልን የምትገለባብጡ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም።
19. አሁንም ልከህ እስራኤልን ሁሉ፥ በኤልዛቤልም ማዕድ የሚበሉትን አራት መቶ አምሳ የበኣልን ነቢያት፥ አራት መቶም የማምለኪያ ዐፀድን ነቢያት ወደ እኔ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብ አለ።
20. አክዓብም ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ ልኮ ነቢያቱን ሁሉ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ።
21. ኤልያስም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ። እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ አለ። ሕዝቡም አንዲት ቃል አልመለሱለትም።
22. ኤልያስም ሕዝቡን አለ። ከእግዚአብሔር ነቢያት እኔ ብቻ ቀርቻለሁ፤ የበኣል ነቢያት ግን አራት መቶ አምሳ ሰዎች ናቸው።
23. ሁለት ወይፈኖች ይሰጡን፤ እነርሱም አንድ ወይፈን ይምረጡ፥ እየብልቱም ይቍረጡት፥ በእንጨትም ላይ ያኑሩት፥ በበታቹም እሳት አይጨምሩ፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረዋለሁ፥ በበታቹም እሳት አልጨምርም።
24. እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፥ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፥ እርሱ አምላክ ይሁን። ሕዝቡም ሁሉ። ይህ ነገር መልካም ነው ብለው መለሱ።
25. ኤልያስም የበኣልን ነቢያት። እናንተ ብዙዎች ናችሁና አስቀድማችሁ አንድ ወይፈን ምረጡና አዘጋጁ፤ የአምላካችሁንም ስም ጥሩ፥ በበታችሁም እሳት አትጨምሩ አላቸው።
26. ወይፈኑንም ወስደው አዘጋጁ፥ ከጠዋትም እስከ ቀትር ድረስ። በኣል ሆይ፥ ስማን እያሉ የበኣልን ስም ጠሩ። ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስም አልነበረም፤ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ያሸበሽቡ ነበር።
27. በቀትርም ጊዜ ኤልያስ። አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፤ ምናልባት አሳብ ይዞታል፥ ወይም ፈቀቅ ብሎአል፥ ወይም ወደ መንገድ ሄዶአል፥ ወይም ተኝቶ እንደ ሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል እያለ አላገጠባቸው።
28. በታላቅም ቃል ይጮኹ፥ እንደ ልማዳቸውም ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ገላቸውን በካራና በቀጭኔ ይብዋጭሩ ነበር።
29. ቀትርም ካለፈ በኋላ መሥዋዕተ ሠርክ እስኪደርስ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስና የሚያደምጥም አልነበረም።
30. ኤልያስም ሕዝቡን ሁሉ። ወደ እኔ ቅረቡ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ። ፈርሶ የነበረውንም የእግዚአብሔርን መሠዊያ አበጀ።
31. ኤልያስም። ስምህ እስራኤል ይሆናል የሚል የእግዚአብሔር ቃል እንደ ደረሰለት እንደ ያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወሰደ።
32. ከድንጋዮችም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚያዝ ጕድጓድ ቈፈረ።
33. እንጨቱንም በተርታ አደረገ፥ ወይፈኑንም በብልት በብልቱ ቈረጠ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረና።
34. አራት ጋን ውኃ ሙሉ በሚቃጠለው መሥዋዕትና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ አሉ። ደግሞም። ድገሙ አለ፤ እነርሱም ደገሙ። እርሱም። ሦስተኛ አድርጉ አለ፤ ሦስተኛም አደረጉ።
35. ውኃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ደግሞም ጕድጓዱን በውኃ ሞላው።
36. መሥዋዕተ ሠርክ በሚቀርብበት ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቀርቦ። አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ።
37. አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፥ አቤቱ፥ ስማኝ አለ።
38. የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፥ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች።
39. ሕዝቡም ሁሉ ያንን ባዩ ጊዜ በግምባራቸው ተደፍተው። እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው አሉ።
40. ኤልያስም። ከበኣል ነቢያት አንድ ሰው እንዳያመልጥ ያዙ አላቸው። ያዙአቸውም፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ ወስዶ በዚያ አሳረዳቸው።
41. ኤልያስም አክዓብን። የዝናቡ ውሽንፍር እጅግ ነውና ተነሥተህ ውጣ፥ ብላም ጠጣም አለው።
42. አክዓብም ሊበላና ሊጠጣ ወጣ፤ ኤልያስም ወደ ቀርሜሎስ አናት ወጣ፤ ፊቱንም በጕልበቱ መካከል አድርጎ በግምባሩ ተደፋ።
43. ብላቴናውንም። ወጥተህ ወደ ባሕሩ ተመልከት አለው። ወጥቶም ተመልክቶም። ምንም የለም አለ። እርሱም። ሰባት ጊዜ ተመላለስ አለው። ብላቴናውም ሰባት ጊዜ ተመላለሰ።
44. በሰባተኛውም ጊዜ። እነሆ፥ የሰው እጅ የምታህል ታናሽ ደመና ከባሕር ወጥች አለ። እርሱም። ወጥተህ አክዓብን። ዝናብ እንዳይከለክልህ ሰረገላን ጭነህ ውረድ በለው አለ።
45. ከጥቂትም ጊዜ በኋላ ሰማዩ ከደመናውና ከነፋሱ የተነሣ ጨለመ፥ ብዙም ዝናብ ሆነ፤ አክዓብም በሰረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ።
46. የእግዚአብሔርም እጅ በኤልያስ ላይ ነበረች፤ ወገቡንም አሸንፍጦ ወደ ኢይዝራኤል እስኪገባ ድረስ በአክዓብ ፊት ይሮጥ ነበር።

  1Kings (18/22)