← 1Kings (14/22) → |
1. | በዚያም ወራት የኢዮርብዓም ልጅ አብያ ታመመ። |
2. | ኢዮርብዓምም ሚስቱን። ተነሺ፥ የኢዮርብዓምም ሚስት እንደ ሆንሽ እንዳትታወቂ ልብስሽን ለውጪና ወደ ሴሎ ሂጂ፤ እነሆ፥ በዚህ ሕዝብ ላይ እንድነግሥ የነገረኝ ነቢዩ አኪያ በዚያ አለ። |
3. | በእጅሽም አሥር እንጀራና እንጎቻዎች አንድም ምንቸት ማር ይዘሽ ወደ እርሱ ሂጂ፤ በልጁም የሚሆነውን ይነግርሻል አላት። |
4. | የኢዮርብዓምም ሚስት እንዲሁ አደረገች፥ ተነሥታም ወደ ሴሎ ሄደች፤ ወደ አኪያም ቤት መጣች። አኪያም ስለ መሸምገሉ ዓይኖቹ ፈዝዘው ነበርና፤ ማየት አልቻለም። |
5. | እግዚአብሔርም አኪያን። እነሆ፥ ስለ ታመመው ልጅዋ ትጠይቅህ ዘንድ የኢዮርብዓም ሚስት ትመጣለች፤ ሌላ ሴትም መስላ ተሰውራለችና በገባች ጊዜ እንዲህና እንዲህ በላት አለው። |
6. | እርስዋም በደጅ ስትገባ አኪያ የእግርዋን ኮቴ ሰማ፥ እንዲህም አለ። የኢዮርብዓም ሚስት ሆይ፥ ግቢ፤ ስለ ምንስ ሌላ ሴት መሰልሽ? እኔም ብርቱ ወሬ ይዤ ተልኬልሻለሁ። |
7. | ሂጂ፥ ለኢዮርብዓምም እንዲህ በዪው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከሕዝብ መካከል ለይቼ ከፍ አድርጌህ ነበር፥ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌህ ነበር፥ |
8. | ከዳዊትም ቤት መንግሥቱን ቀድጄ ሰጥቼህ ነበር፤ ነገር ግን በፍጹም ልቡ እንደ ተከተለኝ፥ በፊቴም ቅን ነገር ብቻ እንዳደረገ፥ ትእዛዜንም እንደ ጠበቀ እንደ ባሪያዬ እንደ ዳዊት አልሆንህም። |
9. | ከአንተም አስቀድመው ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ክፉ ሠራህ፤ ታስቈጣኝም ዘንድ ሄደህ ሌሎችን አማልክትና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች አደረግህ፥ ወደ ኋላህም ጣልኸኝ። |
10. | ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢዮርብዓም ቤት ላይ መከራ አመጣለሁ፥ ከኢዮርብአምም በእስራኤል ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ እቈርጣለሁ፤ ሰውም ፋንድያን እስኪጠፋ ድረስ እንደሚጠርግ እኔ የኢዮርብዓምን ቤት ፈጽሜ እጠርጋለሁ። |
11. | ከኢዮርብዓምም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። |
12. | እንግዲህ ተነሥተሽ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እግርሽም ወደ ከተማ በገባ ጊዜ ልጁ ይሞታል። |
13. | እስራኤልም ሁሉ ያለቅሱለታል፥ ይቀብሩትማል፤ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ በኢዮርብዓም ቤት በዚህ ልጅ መልካም ነገር ተገኝቶበታልና ከኢዮርብዓም እርሱ ብቻ ይቀበራል። |
14. | እግዚአብሔርም ደግሞ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ያስነሣል፤ እርሱም በዚያ ዘመን የኢዮርብዓምን ቤት ያጠፋል። |
15. | በዚያ ጊዜም ሸምበቆ በውኃ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ እግዚአብሔር እንዲሁ እስራኤልን ይመታል፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ የማምለኪያ ዐፀድ ተክለዋልና ለአባቶቻቸው ከሰጣቸው ከዚች ከመልካሚቱ ምድር እስራኤልን ይነቅላል፥ በወንዙም ማዶ ይበትናቸዋል። |
16. | ስለ በደለውና እስራኤልንም ስላሳተበት ስለ ኢዮርብዓም ኃጢአት እስራኤልን ይጥላል። |
17. | የኢዮርብዓምም ሚስት ተነሥታ ሄደች፥ ወደ ቴርሳ መጣች፤ ወደ ቤቱም መድረክ በገባች ጊዜ ልጁ ሞተ። |
18. | በባሪያውም በነቢዩ በአኪያ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስራኤል ሁሉ ቀበሩት አለቀሱለትም። |
19. | የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ እንዴት እንደ ተዋጋ፥ እንዴትም እንደ ነገሠ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። |
20. | ኢዮርብዓምም የነገሠበት ዘመን ሀያ ሁለት ዓመት ነበረ፤ ከአባቶቹም ጋር አንቀላፋ፥ ልጁም ናዳብ በፋንታው ነገሠ። |
21. | የሰሎሞንም ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ ሮብዓምም ንጉሥ በሆነ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጉልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም አሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም ናዕማ ነበረ፤ እርስዋም አሞናዊት ነበረች። |
22. | ይሁዳም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ፤ አባቶቻቸውም ከሠሩት ሁሉ ይልቅ አብዝተው በሠሩት ኃጢአት አስቈጡት። |
23. | እነርሱም ደግሞ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ ቅጠሉ ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች መስገጃዎችንና ሐውልቶችን የማምለኪያ ዐፀዶችንም ለራሳቸው ሠሩ። |
24. | በምድርም ውስጥ ሰዶማውያን ነበሩ፤ ከእስራኤልም ልጆች ፊት እግዚአብሔር ያሳደዳቸውን የአሕዛብን ርኵሰት ሁሉ ያደርጉ ነበር። |
25. | ሮብዓምም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ መጣ። |
26. | የእግዚአብሔርም ቤት መዛግብትንና የንጉሥ ቤት መዛግብትን ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ሰሎሞንም የሠራውን የወርቁን ጋሻ ሁሉ ወሰደ። |
27. | ንጉሡም ሮብዓም በፋንታው የናስ ጋሾችን ሠራ፥ የንጉሥንም ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቆች እጅ አኖራቸው። |
28. | ንጉሡም ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲገባ ዘበኞች ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር። |
29. | የቀረውም የሮብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? |
30. | በዘመኑም ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ሰልፍ ነበረ። |
31. | ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም አብያም በፋንታው ነገሠ። a |
← 1Kings (14/22) → |