| ← 1Kings (10/22) → |
| 1. | የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። |
| 2. | በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። |
| 3. | ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም። |
| 4. | የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥ |
| 5. | የማዕዱንም መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ነፍስ አልቀረላትም። |
| 6. | ንጉሡንም አለችው። ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። |
| 7. | እኔም መጥቼ በዓይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ እነሆም፥ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል። |
| 8. | በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች ናቸው። |
| 9. | አንተን የወደደ፥ በእስራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን፤ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘላለም ወድዶታልና ስለዚህ ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ። |
| 10. | ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቱ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር። |
| 11. | ከኦፊርም ወርቅ ያመጡ የኪራም መርከቦች እጅግ ብዙ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቍ ከኦፊር አመጡ። |
| 12. | ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት መከታ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እስከ ዛሬም ድረስ እንደዚያ ያለ የሰንደል እንጨት ከቶ አልመጣም አልታየምም። |
| 13. | ንጉሡም ሰሎሞን፥ በገዛ እጁ ከሰጣት ሌላ፥ የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ከባሪያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ሄደች። |
| 15. | ግብርም የሚያስገብሩ ሰዎች ነጋዴዎችም የዓረብም ነገሥታት ሁሉ የምድርም ሹማምት ከሚያወጡት ሌላ፥ በየዓመቱ ለሰሎሞን የሚመጣለት የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ። |
| 16. | ንጉሡም ሰሎሞን ከጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላበሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበረ። |
| 17. | ከጥፍጥፍም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት ምናን ነበረ፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው። |
| 18. | ንጉሡም ደግሞ ከዝሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፥ በጥሩም ወርቅ ለበጠው። |
| 19. | ወደ ዙፋንም የሚያስሄዱ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ በስተ ኋላውም ያለው የዙፋኑ ራስ ክብ ነበረ፤ በዚህና በዚያ በመቀመጫው አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፥ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር። |
| 20. | በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ አሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። |
| 21. | ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ ወርቅ ነበረ፥ የሊባኖስ ዱር የተባለውም ቤት ዕቃ ሁሉ ጥሩ ወርቅ እንጂ ብር አልነበረም። በሰሎሞን ዘመን ብር ከቶ አይቈጠርም ነበር። |
| 22. | ለንጉሡም ከኪራም መርከቦች ጋር የተርሴስ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር፥ የዝሆንም ጥርስ፥ ዝንጀሮና ዝንጕርጕር ወፍ ይዘው ይመጡ ነበር። |
| 23. | ንጉሡም ሰሎሞን በባለጠግነትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ በልጦ ነበር። |
| 24. | ምድርም ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረለትን ጥበቡን ይሰማ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ይመኝ ነበር። |
| 25. | ከእነርሱም እያንዳንዱ በዓመቱ በዓመቱ ገጸ በረከቱን፥ የብርና የወርቅ ዕቃ፥ ልብስና የጦር መሣሪያ፥ ሽቱም፥ ፈረሶችና በቅሎች እየያዘ ይመጣ ነበር። |
| 26. | ሰሎሞንም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፤ አንድ ሺህ አራት መቶ ሰረገሎች፥ አሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፥ በሰረገሎችም ከተሞች ከንጉሡም ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። |
| 27. | ንጉሡም ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። |
| 28. | ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አገር አስመጣ፤ የንጉሡም ነገዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር። |
| 29. | አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ አምሳ ብር ከግብጽ ይወጣ ነበር። እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ በእጃቸው ያወጡላቸው ነበር። a |
| ← 1Kings (10/22) → |