← 1John (4/5) → |
1. | ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና። |
2. | የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ |
3. | ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። |
4. | ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችኋቸውማል፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና። |
5. | እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል። |
6. | እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን። |
7. | ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። |
8. | ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። |
9. | በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። |
10. | ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። |
11. | ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። |
12. | እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል። |
13. | ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን። |
14. | እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን። |
15. | ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። |
16. | እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል። |
17. | በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና። |
18. | ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። |
19. | እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። |
20. | ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? |
21. | እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን። |
← 1John (4/5) → |