| ← 1Corinthians (8/16) → |
| 1. | ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋም፥ ሁላችን እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል። |
| 2. | ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ |
| 3. | ማንም ግን እግዚአብሔርን ቢወድ እርሱ በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነው። |
| 4. | እንግዲህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት፥ ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደ ሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። |
| 5. | መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥ |
| 6. | ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን። |
| 7. | ነገር ግን ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ አይገኝም፤ አንዳንዶች ግን ጣዖትን እስከ አሁን ድረስ ስለ ለመዱ። ለጣዖት የተሠዋ ነው ብለው ይበላሉና ሕሊናቸው ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል። |
| 8. | መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም። |
| 9. | ዳሩ ግን ይህ መብታችሁ ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ። |
| 10. | አንተ እውቀት ያለህ በጣዖት ቤት በማዕድ ስትቀመጥ አንድ ሰው ቢያይህ፥ ደካማ ሰው ቢሆን ለጣዖት የተሠዋውን ለመብላት ሕሊናው አይታነጽበትምን? |
| 11. | በአንተ እውቀትም ይህ ደካማ ይጠፋል፥ እርሱም ክርስቶስ የሞተለት ወንድም ነው። |
| 12. | እንዲህም ወንድሞችን እየበደላችሁ ደካማም የሆነውን ሕሊናቸውን እያቆሰላችሁ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። |
| 13. | ስለዚህም መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፥ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም። |
| ← 1Corinthians (8/16) → |