| ← 1Corinthians (4/16) → |
| 1. | እንዲሁ ሰው እኛን እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና እንደ እግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች ይቍጠረን። |
| 2. | እንደዚህም ሲሆን፥ በመጋቢዎች ዘንድ የታመነ ሆኖ መገኘት ይፈለጋል። |
| 3. | ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ |
| 4. | በራሴ ላይ ምንም አላውቅምና፥ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ እኔን የሚፈርድ ግን ጌታ ነው። |
| 5. | ስለዚህም በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል። |
| 6. | ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ። ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። |
| 7. | አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? |
| 8. | አሁን ጠግባችኋል፤ አሁንስ ባለ ጠጎች ሆናችኋል፤ ያለ እኛ ነግሣችኋል፤ እኛ ደግሞ ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ መልካም ይሆን ነበር። |
| 9. | ለዓለም ለመላእክትም ለሰዎችም መጫወቻ ሆነናልና፤ እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሁሉ ይልቅ የኋለኞች እንዳደረገን ይመስለኛልና። |
| 10. | እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን እናንተ ግን ኃይለኞች ናችሁ፤ እናንተ የከበራችሁ ናችሁ እኛ ግን የተዋረድን ነን። |
| 11. | እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ |
| 12. | በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ |
| 13. | እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል። |
| 14. | እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም። |
| 15. | በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና። |
| 16. | እንግዲህ እኔን የምትመስሉ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። |
| 17. | ስለዚህ የምወደውንና የታመነውን በጌታ ልጄ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልኬላችኋለሁ፥ እኔም በየስፍራው በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደማስተምር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚሆነውን መንገዴን እርሱ ያሳስባችኋል። |
| 18. | አንዳንዱ ግን ወደ እናንተ የማልመጣ እየመሰላቸው የታበዩ አሉ፤ |
| 19. | ነገር ግን ጌታ ቢፈቅድ ፈጥኜ ወደ እናንተ እመጣለሁ፥ የትዕቢተኞችንም ኃይል አውቃለሁ እንጂ ቃላቸውን አይደለም፤ |
| 20. | የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ነው እንጂ በቃል አይደለምና። |
| 21. | ምን ትወዳላችሁ? በበትር ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ ልምጣባችሁን? |
| ← 1Corinthians (4/16) → |