1Corinthians (16/16)    

1. ለቅዱሳንም ገንዘብን ስለ ማዋጣት፥ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደነገግሁት እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።
2. እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያን ጊዜ እንዳይሆን፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ።
3. ስመጣም ማናቸውም ቢሆኑ የታመኑ የሚመስሉአችሁ ሰዎች ቸርነታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሱ ዘንድ ደብዳቤ ሰጥቼ እልካቸዋለሁ፤
4. እኔ ደግሞ ልሄድ የሚገባኝ ብሆን ከእኔ ጋር አብረው ይሄዳሉ።
5. በመቄዶንያም ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመቄዶንያ አድርጌ አልፋለሁና፤
6. እናንተም ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጉዞዬ እንድትረዱኝ ምናልባት በእናንተ ዘንድ እቆይ ወይም እከርም ይሆናል።
7. አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጎበኛችሁ አልወድምና፤ ጌታ ቢፈቅደው የሆነውን ዘመን በእናንተ ዘንድ ልሰነብት ተስፋ አደርጋለሁና።
8. በኤፌሶን ግን እስከ በዓለ ኀምሳ ድረስ እሰነብታለሁ።
9. ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛልና ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው።
10. ጢሞቴዎስም የመጣ እንደ ሆነ በእናንተ ዘንድ ያለ ፍርሃት እንዲኖር ተጠንቀቁ፤ እንደ እኔ ደግሞ የጌታን ሥራ ይሠራልና፤ እንግዲህ ማንም አይናቀው።
11. ነገር ግን ከወንድሞቹ ጋር እጠብቀዋለሁና ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ በሰላም በጉዞው እርዱት።
12. ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስ ግን ከወንድሞቹ ጋር ወደ እናንተ ሊሄድ እጅግ አድርጌ ለምኜው ነበር፤ ዛሬም ለመምጣት ከቶ ፈቃድ አልነበረውም፥ ሲመቸው ግን ይመጣል።
13. ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ።
14. በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን።
15. ወንድሞች ሆይ፥ የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች የአካይያ በኩራት እንደ ሆኑ ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ፤
16. እንደ እነርሱ ላሉትና አብሮ ለሚሠራ ለሚደክምም ሁሉ እናንተም እንድትገዙ እለምናችኋለሁ።
17. በእስጢፋኖስና በፈርዶናጥስ በአካይቆስም መምጣት ደስ ይለኛል፥ እናንተ ስለሌላችሁ የጎደለኝን ፈጽመዋልና፤ መንፈሴንና መንፈሳችሁን አሳርፈዋልና።
18. እንግዲህ እንደነዚህ ያሉትን እወቁአቸው።
19. የእስያ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ በቤታቸው ካለች ቤተ ክርስቲያን ጋር በጌታ እጅግ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
20. ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ።
21. እኔ ጳውሎስ ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ ጽፌአለሁ።
22. ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፥ ና።
23. የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
24. ፍቅሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሁላችሁ ጋር ነው። አሜን።

  1Corinthians (16/16)