1Chronicles (7/29)  

1. የይሳኮርም ልጆች፥ ቶላ፥ ፉዋ፥ ያሱብ ሺምሮን፥ አራት ናቸው።
2. የቶላም ልጆች፥ ኦዚ፥ ራፋያ፥ ይሪኤል፥ የሕማይ፥ ይብሣም፥ ሽሙኤል፥ የአባታቸው የቶላ ቤት አለቆች፥ በትውልዳቸው ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ በዳዊት ዘመን ቍጥራቸው ሀያ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበረ።
3. የኦዚም ልጆች ይዝረሕያ፤ የይዝረሕያም ልጆች ሚካኤል፥ አብድዩ፥ ኢዮኤል፥ ይሺያ አምስት ናቸው፤ ሁሉም አለቆች ነበሩ።
4. ከእነርሱም ጋር በየትውልዳቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች ለሰልፍ የተዘጋጁ የሠራዊት ጭፍሮች ነበሩ፤ ብዙም ሴቶችና ልጆች ነበሩአቸውና ሠላሳ ስድስት ሺህ ነበሩ።
5. ወንድሞቻቸውም በይሳኮር ወገኖች ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች በትውልዳቸው ሁሉ የተቈጠሩ ሰማኒያ ሰባት ሺህ ነበሩ።
6. የብንያም ልጆች ቤላ፥ ቤኬር፥ ይዲኤል ሦስት ነበሩ።
7. የቤላም ልጆች፥ ኤሴቦን፥ ኦዚ፥ ዑዝኤል፥ ኢያሪሙት፥ ዒሪ፥ አምስት ነበሩ፤ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ፤ በትውልድ የተቈጠሩ ሀያ ሁለት ሺህ ሠላሳ አራት ነበሩ።
8. የቤኬርም ልጆች፤ ዝሚራ፥ ኢዮአስ፥ አልዓዛር፥ ኤልዮዔናይ፥ ዖምሪ፥ ኢያሪሙት፥ አብያ፥ ዓናቶት፥ ዓሌሜት፤ እነዚህ ሁሉ የቤኬር ልጆች ነበሩ።
9. በየትውልዳቸው መዝገብ የተቈጠሩ፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ሀያ ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
10. የይዲኤልም ልጅ ቢልሐን ነበረ፤ የቢልሐንም ልጆች የዑስ፥ ብንያም፥ ኤሁድ፥ ክንዓና፥ ዜታን፥ ተርሴስ፥ አኪሳአር ነበሩ።
11. እነዚህ ሁሉ የይዲኤል ልጆች ነበሩ፤ በየአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ጭፍራ እየሆኑ ወደ ሰልፍ የሚወጡ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች አሥራ ሰባት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
12. ደግሞም ሳፊን፥ ሑፊም የዒር ልጆች፥ ሑሺም የአሔር ልጆችም ነበሩ።
13. የንፍታሌም ልጆች፥ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጽር፥ ሺሌም፥ የባላ ልጆች ነበሩ።
14. የምናሴ ልጆች ሶርያይቱ ቁባቱ የወለደችለት እሥርኤልና የገለዓድ አባት ማኪር ናቸው።
15. ማኪርም ከሑፊምና ከሳፊን ወገን ሚስት አገባ፤ የእኅትዋም ስም መዓካ ነበረ፤ የሁለተኛውም ስም ሰለጰአድ ነበረ፤ ለሰለጰዓድም ሴቶች ልጆች ነበሩት።
16. የማኪርም ሚስት መዓካ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ፋሬስ ብላ ጠራችው፤ የወንድሙም ስም ሱሮስ ነበረ፤ ልጆቹም ኡላም፥ ራቄም ነበሩ።
17. የኡላምም ልጅ ባዳን ነበረ፤ እነዚህ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጆች ነበሩ።
18. እኅቱ መለኬት ኢሱድን፥ አቢዔዝርን፥ መሕላን ወለደች።
19. የሸሚዳም ልጆች አሒያን፥ ሴኬም፥ ሊቅሒ፥ አኒዓም ነበሩ።
20. የኤፍሬም ልጆች፤ ሹቱላ፥ ልጁ ባሬድ፥ ልጁ ታሐት፥ ልጁ ኤልዓዳ፥ ልጁ ታሐት፥ ልጁ ዛባድ፥ ልጁ ሽቱላ፥
21. የአገሩም ተወላጆች የጌት ሰዎች ከብቶቻቸውን ሊወስዱ ወርደው ነበርና የገደሉአቸው ልጆቹ ኤድርና ኤልዓድ ነበሩ።
22. አባታቸውም ኤፍሬም ብዙ ቀን አለቀሰ፥ ወንድሞቹም ሊያጽናኑት መጡ።
23. ወደ ሚስቱም ገባ፥ አረገዘችም፥ ወንድ ልጅም ወለደች፤ በቤቱም መከራ ሆኖአልና ስሙ በሪዓ ብሎ ጠራው።
24. ሴት ልጁም ታችኛውንና ላይኛውን ቤትሖሮንንና ኡዜንሼራን የሠራች ሲአራ ነበረች።
25. ወንዶች ልጆቹም ፋፌ፥ ሬሴፍ፥ ልጁ ቴላ፥
26. ልጁ ታሐን፥ ልጁ ለአዳን፥ ልጁ ዓሚሁድ፥ ልጁ ኤሊሳማ፥
27. ልጁ ነዌ፥ ልጁ ኢያሱ።
28. ግዛታቸውና ማደሪያቸው ቤቴልና መንደሮችዋ፥ በምሥራቅም በኩል ነዓራን፥ በምዕራብም በኩል ጌዝርና መንደሮችዋ፥ ደግሞ ሴኬምና መንደሮችዋ እስከ ጋዛና እስከ መንደሮችዋ ድረስ፥
29. በምናሴም ልጆች ዳርቻ ቤትሳንና መንደሮችዋ፥ ታዕናክና መንደሮችዋ፥ መጊዶና መንደሮችዋ፥ ዶርና መንደሮችዋ ነበሩ፤ በእነዚህ የእስራኤል ልጅ የዮሴፍ ልጆች ተቀመጡ።
30. የአሴር ልጆች ዪምና፥ የሱዋ፥ የሱዊ፥ በሪዓ፥ እኅታቸውም ሤራሕ።
31. የበሪዓም ልጆች፤ ሔቤር፥ የቢርዛዊት አባት የነበረው መልኪኤል።
32. ሔቤርም ያፍሌጥን፥ ሳሜንር፥ ኮታምን፥ እኅታቸውንም ሶላን ወለደ።
33. የያፍሌጥም ልጆች ፋሴክ፥ ቢምሃል፥ ዓሲት ነበሩ፤ እነዚህ የያፍሌጥ ልጆች ነበሩ።
34. የሳሜርም ልጆች አኪ፥ ሮኦጋ፥ ይሑባ፥ አራም ነበሩ።
35. የወንድሙም የኤላም ልጆች ጾፋ፥ ይምና፥ ሰሌስ፥ ዓማል ነበሩ።
36. የጾፋም ልጆች ሱዋ፥ ሐርኔፍር፥
37. ሦጋል፥ ቤሪ፥ ይምራ፥ ቤጼር፥ ሆድ፥ ሳማ፥ ሰሊሳ፥ ይትራን፥ ብኤራ ነበሩ።
38. የዬቴር ልጆች ዮሮኒ፥ ፊስጳ፥ አራ ነበሩ።
39. የዑላ ልጆች ኤራ፥ ሐኒኤል፥ ሪጽያ ነበሩ።
40. እነዚህ ሁሉ የአሴር ልጆች፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ የተመረጡ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች፥ የመኳንንቱ አለቆች ነበሩ። በትውልዳቸውም በሰልፍ ለመዋጋት የተቈጠሩ ሀያ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ።

  1Chronicles (7/29)