← 1Chronicles (26/29) → |
1. | በረኞችም እንደዚህ ተመደቡ፤ ከቆሬያውያን ከአሳፍ ልጆች የቆሬ ልጅ ሜሱላም። |
2. | ሜሱላም ልጆች ነበሩት፤ በኵሩ ዘካርያስ፥ ሁለተኛው ይዲኤል፥ ሦስተኛው ዮዛባት፥ |
3. | አራተኛው የትኒኤል፥ አምስተኛው ኤላም፥ ስድስተኛው ይሆሐናን፥ ሰባተኛው ኤሊሆዔናይ። |
4. | እግዚአብሔርም ባርኮታልና ዖቤድኤዶም ልጆች ነበሩት፤ በኵሩ ሸማያ፥ ሁለተኛው ዮዛባት፥ ሦስተኛው ኢዮአስ፥ አራተኛው ሣካር፥ አምስተኛው ናትናኤል፥ |
5. | ስድስተኛው ዓሚኤል፥ ሰባተኛው ይሳኮር፥ ስምንተኛው ፒላቲ። |
6. | ለልጁም ለሸማያ ደግሞ ልጆች ተወለዱለት፤ ጽኑዓንም ኃያላን ነበሩና በአባታቸው ቤት ሠለጠኑ። |
7. | ለሸማያ ልጆች ዖትኒ፥ ራፋኤል፥ ዖቤድ፥ ወንድሞቹም ኃያላን የነበሩ ኤልዛባድ፥ ኤልሁ፥ ሰማክያ። |
8. | እነዚህ ሁሉ የዖቤድኤዶም ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ለማገልገል ኃያላን የነበሩ የዖቤድኤዶም ልጆች ስድሳ ሁለት ነበሩ። |
9. | ለሜሱላም ኃያላን የነበሩ አሥራ ስምንት ልጆችና ወንድሞች ነበሩት። |
10. | ከሜራሪም ልጆች ለነበረው ለሖሳ ልጆች ነበሩት፤ አለቃውም ሽምሪ ነበረ፤ በኵር አልነበረም፥ አባቱ ግን አለቃ አደረገው፤ |
11. | ሁለተኛውም ኬልቅያስ፥ ሦስተኛው ጥበልያ፥ አራተኛው ዘካርያስ ነበረ፤ የሖሳ ልጆችና ወንድሞች ሁሉ አሥራ ሦስት ነበሩ። |
12. | እንደ ወንድሞቻቸው ሆነው በእግዚአብሔር ቤት ያገለግሉ ዘንድ የበረኞች የአለቆች ሰሞነኞች እነዚህ ነበሩ። |
13. | በበሩም ሁሉ ያገለግሉ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች ታናሹና ታላቁ ተካክለው ዕጣ ተጣጣሉ። |
14. | በምሥራቅም በኩል ዕጣ ለሰሌምያ ወደቀ። ለልጁም ብልህ መካር ለሆነው ለዘካርያስ ዕጣ ጣሉ፤ ዕጣውም በሰሜን በኩል ወጣ። |
15. | ለዖቤድኤዶም በደቡብ በኩል፥ ለልጆቹም ለዕቃ ቤቱ ዕጣ ወጣ። |
16. | ለሰፊንና ለሖሳ በምዕራብ በኩል፥ በዐቀበቱም መንገድ ባለው በሸሌኬት በር በኩል ጥበቃ ከጥበቃ ላይ ዕጣ ወጣ። |
17. | በምሥራቅ በኩል ስድስት ሌዋውያን ነበሩ፤ በሰሜን በኩል ለየዕለቱ አራት፥ በደቡብ በኩል ለየዕለቱ አራት፥ ለዕቃ ቤቱም ሁለት ሁለት ነበሩ። |
18. | በምዕራብ በኩል በፈርባር መንገድ ላይ አራት፥ በፈርባርም አጠገብ ሁለት ነበሩ። |
19. | ከቆሬና ከሜራሪ ልጆች የነበሩ የበረኞች ሰሞን ይህ ነበረ። |
20. | ከሌዋውያን አኪያ በእግዚአብሔር ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብትና በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ላይ ተሾሞ ነበር። |
21. | የለአዳን ልጆች፤ ለለአዳን የሆኑ የጌድሶናውያን ልጆች፥ ለጌድሶናዊ ለለአዳን የሆኑ የአባቶች ቤቶች አለቆች ይሒኤሊ፤ |
22. | የይሒኤሊ ልጆች፤ በእግዚአሔር ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብት ላይ የነበሩ ዜቶም፥ ወንድሙም ኢዩኤል። |
23. | ከእንበረማውያን፥ ከይስዓራውያን፥ ከኬብሮናውያን፥ ከዑዝኤላውያን፤ |
24. | የሙሴ ልጅ የጌርሳም ልጅ ሱባኤል በቤተ መዛግብት ላይ ተሾሞ ነበር። |
25. | ወንድሞቹም፤ ከአልዓዛር ልጁ ረዓብያ፥ ልጁም የሻያ፥ ልጁም ኢዮራም፥ ልጁም ዝክሪ፥ ልጁም ሰሎሚት መጡ። |
26. | ይህ ሰሎሚትና ወንድሞቹ ንጉሡ ዳዊትና የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች የሠራዊቱም አለቆች፥ በቀደሱት በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ሁሉ ላይ ተሾመው ነበር። |
27. | በሰልፍም ከተገኘው ምርኮ የእግዚአብሔርን ቤት ለማበጀት ቀደሱ። |
28. | ባለ ራእዩም ሳሙኤል፥ የቂስም ልጅ ሳኦል፥ የኔርም ልጅ አበኔር፥ የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የቀደሱት ንዋየ ቅድሳት ሁሉ ከሰሎሚትና ከወንድሞቹ እጅ በታች ነበረ። |
29. | ከይስዓራውያን ከናንያና ልጆቹ ሹማምትና ፈራጆች ይሆኑ ዘንድ በውጭው ሥራ በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር። |
30. | ከኬብሮናውያን ሐሸብያና ወንድሞቹ፥ ጽኑዓን የነበሩት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥ ለእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ ለንጉሡም አገልግሎት በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ባለው በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር። |
31. | ከኬብሮናውያንም እንደ አባቶች ቤቶች ትውልዶች የኬብሮናውያን አለቃ ይርያ ነበረ። ዳዊት በነገሠ በአርባኛው ዓመት ይፈልጉአቸው ነበር፤ በእነርሱም መካከል በገለዓድ ኢያዜር ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ተገኙ፤ |
32. | ወንድሞቹም ጽኑዓን የነበሩት የአባቶች ቤቶች አለቆች ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። ንጉሡም ዳዊት ለእግዚአብሔር ጉዳይ ሁሉና ለንጉሡ ጉዳይ በሮቤላውያንና በጋዳውያን በምናሴም ነገድ እኵሌታ ላይ ሹሞች አደረጋቸው። |
← 1Chronicles (26/29) → |