1Chronicles (21/29)  

1. ሰይጣንም በእስራኤል ላይ ተነሣ፥ እስራኤልንም ይቈጥር ዘንድ ዳዊትን አንቀሳቀሰው።
2. ዳዊትም ኢዮአብንና የሕዝቡን አለቆች። ሂዱ፥ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ እስራኤልን ቍጠሩ፥ ድምራቸውንም አውቅ ዘንድ አስታውቁኝ አላቸው።
3. ኢዮአብም። እግዚአብሔር ሕዝቡን በአሁኑ ላይ መቶ እጥፍ ይጨምር፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ሁሉ የጌታዬ ባሪያዎች አይደሉምን? ይህን ነገር ጌታዬ ለምን ይሻል? በእስራኤል ላይ በደል ስለ ምን ያመጣል?
4. ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብ ላይ አሸነፈ፤ ኢዮአብም ወጥቶ በእስራኤል ሁሉ ላይ ተዘዋወረ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ።
5. ኢዮአብም የቈጠራቸውን የሕዝቡን ድምር ለዳዊት ሰጠ፤ ከእስራኤልም ሁሉ አንድ ሚሊዮን ከመቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ፤ ከይሁዳም አራት መቶ ሰባ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎችን አገኘ።
6. የንጉሡ ትእዛዝ ግን በኢዮአብ ዘንድ የተጠላ ነበርና ሌዊና ብንያም ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም።
7. ከዚህም ነገር የተነሣ እግዚአብሔር ተቈጣ፥ እስራኤልንም ቀሠፈ።
8. ዳዊትም እግዚአብሔርን። ይህን በማድረግ እጅግ በድያለሁ፤ አሁን ግን ታላቅ ስንፍና አድርጌአለሁና የባሪያህን ኃጢአት ታስወግድ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው።
9. እግዚአብሔርም ለዳዊት ባለ ራእይ ለጋድ።
10. ሂድ፥ ለዳዊት። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሦስቱን ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፤ አደርግብህ ዘንድ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ ብለህ ንገረው ብሎ ተናገረው።
11. ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የምትወድደውን ምረጥ፤
12. የሦስት ዓመት ራብ፥ ወይም ሦስት ወር የጠላቶችህ ሰይፍ እንዲያገኝህ ከጠላቶችህ መሰደድን፥ ወይም ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ ቸነፈርም በምድር ላይ መሆንን፥ የእግዚአብሔርም መልአክ በእስራኤል ምድር ሁሉ ማጥፋትን ምረጥ፤ አሁንም ለላከኝ ምን እንድመልስ ተመልከት አለው።
13. ዳዊትም ጋድን። እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ ልውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ አለው።
14. እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቸነፈርን ሰደደ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰዎች ወደቁ።
15. እግዚአብሔርም ያጠፋት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም መልአክን ሰደደ፤ ሊያጠፋትም በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር አይቶ ስለ ክፉው ነገር ተጸጸተ፥ የሚያጠፋውንም መልአክ። በቃህ፤ አሁን እጅህን መልስ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።
16. ዳዊትም ዓይኖቹን አነሣ፤ የእግዚአብሔር መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትም ሽማግሌዎችም ማቅ ለብሰው በግምባራቸው ተደፉ።
17. ዳዊትም እግዚአብሔርን። ሕዝቡ ይቈጠር ዘንድ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? የበደልሁና ክፉ የሠራሁ እኔ ነኝ፤ እነዚህ በጎች ግን ምን አድርገዋል? አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን፥ ነገር ግን ይቀሠፍ ዘንድ በሕዝብህ ላይ አትሁን አለው።
18. የእግዚአብሔርም መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ ለዳዊት እንዲነግረው ጋድን አዘዘው።
19. ዳዊትም በእግዚአብሔር ስም እንደ ተናገረው እንደ ጋድ ነገር ወጣ።
20. ኦርናም ዘወር ብሎ መልአኩን አየ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ አራቱ ልጆቹ ተሸሸጉ፤ ኦርናም ስንዴ ያበራይ ነበር።
21. ዳዊትም ወደ ኦርና በመጣ ጊዜ ኦርና ተመልክቶ ዳዊትን አየ፤ ከአውድማውም ወጥቶ ዳዊትን እጅ ሊነሣ በምድር ላይ ተደፋ።
22. ዳዊትም ኦርናን። በላዩ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እሠራ ዘንድ ይህን የአውድማ ስፍራ ስጠኝ፤ በሙሉ ዋጋ ስጠኝ፤ መቅሠፍቱን ከሕዝቡ ይከለከላል አለው።
23. ኦርናም ዳዊትን። ለአንተ ውሰደው፥ ጌታዬ ንጉሡም ደስ የሚያሰኘውን ያድርግ፤ እነሆ፥ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሬዎቹን፥ ለእንጨትም የአውድማውን ዕቃ፥ ከእህልም ቍርባን ስንዴውን እሰጥሃለሁ፤ ሁሉን እሰጣለሁ አለው።
24. ንጉሡም ዳዊት ኦርናን። አይደለም፥ ነገር ግን ለአንተ ያለውን ለእግዚአብሔር አምጥቼ የሚቃጠል መሥዋዕት በከንቱ አላቀርብምና በሙሉ ዋጋ እገዛዋለሁ አለው።
25. ዳዊትም ስለ ስፍራው ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ በሚዛን ለኦርና ሰጠው።
26. ዳዊትም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ጠራ፤ ከሰማይም ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ በእሳት መለሰለት።
27. እግዚአብሔርም መልአኩን አዘዘው፥ ሰይፉንም በአፎቱ ከተተው።
28. በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ እንደ መለሰለት ዳዊት ባየ ጊዜ፥ በዚያ መሥዋዕት ሠዋ።
29. ሙሴም በምድረ በዳ የሠራት የእግዚአብሔር ማደሪያና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ በዚያን ጊዜ በገባዖን ባለው በኮረብታው መስገጃ ነበሩ።
30. ዳዊት ግን የእግዚአብሔርን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደዚያ ይሄድ ዘንድ አልቻለም።

  1Chronicles (21/29)