| ← 1Chronicles (20/29) → |
| 1. | እንዲህም ሆነ፤ በዓመት መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ ኢዮአብ ሠራዊቱን አወጣ፥ የአሞንንም ልጆች አገር አጠፋ፤ መጥቶም ረባትን ከበበ። ዳዊትም በኢየሩሳሌም ቈይቶ ነበር። |
| 2. | ኢዮአብም ረባትን መትቶ አፈረሳት። ዳዊትም የንጉሣቸውን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፥ ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበረ፥ ክቡርም ዕንቍ ነበረበት፥ በዳዊትም ራስ ላይ አስቀመጡት፤ ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። |
| 3. | በውስጥዋም የነበረውን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያ በመጥረቢያም እንዲሠሩ አደረጋቸው። እንዲሁም ዳዊት በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። |
| 4. | ከዚህም በኋላ በጌዝር ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ሆነ፤ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሲፋይን ገደለ። |
| 5. | ደግሞም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፤ የያዒርም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው የጎልያድን ወንድም ለሕሚን ገደለ። |
| 6. | ደግሞ በጌት ላይ ሰልፍ ነበረ፤ ከዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ሁላሁሉ ሀያ አራት ጣቶች ያሉት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ። |
| 7. | እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው። |
| 8. | እነዚያም በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በባሪያዎቹም እጅ ወደቁ። |
| ← 1Chronicles (20/29) → |