| ← 1Chronicles (19/29) → |
| 1. | ከዚህም በኋላ የአሞን ልጆች ንጉሥ ናዖስ ሞተ፥ ልጁም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |
| 2. | ዳዊትም። አባቱ ስላደረገልኝ ወረታ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ልያጽናናው መልእክተኞችን ላከ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ሊያጽናኑት ወደ ሐኖን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ። |
| 3. | የአሞን ልጆች አለቆች ግን ሐኖንን። ዳዊት አባትህን አክብሮ የሚያጽናኑህን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ባሪያዎቹስ አገሪቱን ለመመርመር፥ ለማጥፋት፥ ለመሰለልም ወደ አንተ የመጡ አይደሉምን? አሉት። |
| 4. | ሐኖንም የዳዊትን ባሪያዎች ወስዶ አስላጫቸው፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው። |
| 5. | ወሬኞችም ሄደው በሰዎቹ ላይ የተደረገውን ለዳዊት አስታወቁት። ሰዎቹም በብዙ አፍረዋልና ተቀባዮች ላከ፤ ንጉሡም። ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ አለ። |
| 6. | የአሞንም ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደ ተጠሉ ባዩ ጊዜ ሐኖንና የአሞን ልጆች ከመስጴጦምያ፥ ከአራምመዓካ፥ ከሱባ ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ይቀጥሩ ዘንድ አንድ ሺህ መክሊት ብር ላኩ። |
| 7. | ሠላሳ ሁለትም ሺህ ሰረገሎች የመዓካንም ንጉሥ ሕዝቡንም ቀጠሩ፤ መጥተውም በሜድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአሞንም ልጆች ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ወደ ሰልፍ መጡ። |
| 8. | ዳዊትም ይህ በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ። |
| 9. | የአሞንም ልጆች ወጥተው በከተማይቱ በር አጠገብ ተሰለፉ፤ የመጡትም ነገሥታት ለብቻቸው በሜዳው ላይ በሩ። |
| 10. | ኢዮአብም በፊትና በኋላ ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦችን ሁሉ ለይቶ በሶርያውያን ላይ አሰለፋቸው። |
| 11. | የቀረውንም ሕዝብ ለወንድሙ ለአቢሳ ሰጠው፥ በአሞንም ልጆች ላይ ተሰለፉ። |
| 12. | እርሱም። ሶርያውያን ቢበረቱብኝ እርዳኝ፤ የአሞንም ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ። |
| 13. | አይዞህ፥ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ። |
| 14. | ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ለሰልፍ ወደ ሶርያውያን ፊት ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ። |
| 15. | የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ። ኢዮአብም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። |
| 16. | ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ መልእክተኞች ልከው በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን አስመጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሾፋክ በፊታቸው ነበረ። |
| 17. | ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ መጣባቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊትም በሶርያውያን ላይ በተሰለፈ ጊዜ እነርሱ ከእርሱ ጋር ተዋጉ። |
| 18. | ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞች፥ አርባ ሺህም እግረኞች ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሾፋክን ገደለ። |
| 19. | የአድርአዛርም ባሪያዎች በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ታረቁ፥ ገበሩለትም፤ ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ እንቢ አሉ። |
| ← 1Chronicles (19/29) → |