| ← 1Chronicles (18/29) → |
| 1. | ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፥ አዋረዳቸውም፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ጌትንና መንደሮችዋን ወሰደ። |
| 2. | ሞዓብን መታ፤ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ ግብርም አመጡለት። |
| 3. | ዳዊትም በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት ለመያዝ በሄደ ጊዜ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን እስከ ሃማት ድረስ መታ። |
| 4. | ዳዊትም ከእርሱ አንድ ሺህ ሰረገሎች፥ ሰባት ሺህም ፈረሰኞች፥ ሀያ ሺህም እግረኞች ወሰደ፤ ዳዊት ለመቶ ሰረገሎች የሚሆኑትን ብቻ አስቀርቶ የሰረገሎቹን ፈረሶች ቋንጃ ቆረጠ። |
| 5. | ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን ሀያ ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደለ። |
| 6. | ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ ጭፍሮች አኖረ፤ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል ይሰጠው ነበር። |
| 7. | ዳዊትም ለአድርአዛር ባሪያዎች የነበሩትን የወርቅ ጋሻዎች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞአቸው መጣ። |
| 8. | ከአድርአዛርም ከተሞች ከጢብሐትና ከኩን ዳዊት እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ፤ ከዚህም ሰሎሞን የናሱን ኵሬና ዓምዶች የናሱንም ዕቃ ሠራ። |
| 9. | የሐማትም ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የሱባን ንጉሥ የአድርአዛርን ጭፍራ ሁሉ እንደ መታ ሰማ። |
| 10. | ቶዑም ከአድርአዛር ጋር ሁል ጊዜ ይዋጋ ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ወግቶ ስለመታው ደኅንነቱን ይጠይቅ ዘንድ ይመርቀውም ዘንድ ልጁን አዶራምን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም የወርቅና የብር የናስም ዕቃ ይዞ መጣ። |
| 11. | ንጉሡም ዳዊት ከአሕዛብ ሁሉ ከኤዶምና ከሞዓብ ከአሞንም ልጆች ከፍልስጥኤማውያንም ከአማሌቅም ከማረከው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ደግሞ ለእግዚአብሔር ቀደሰ። |
| 12. | ደግሞ የጽሩያ ልጅ አቢሳ ከኤዶማውያን በጨው ሸለቆ ውስጥ አሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደለ። |
| 13. | በኤዶምያስም ጭፍሮች አኖረ፥ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድል ይሰጠው ነበር። |
| 14. | ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ለሕዝቡም ሁሉ ፍርድንና ጽድቅም አደረገላቸው። |
| 15. | የጽሩያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ። |
| 16. | የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅ፥ የአቤሜሌክም ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ ጸሐፊ ነበረ። |
| 17. | የዮዳሄ ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፤ የዳዊትም ልጆች በንጉሡ አጠገብ አለቆች ነበሩ። |
| ← 1Chronicles (18/29) → |