1Chronicles (14/29)  

1. የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ቤት ይሠሩለት ዘንድ መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም ጠራቢዎችንም አናጢዎችንም ወደ ዳዊት ላከ።
2. ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል መንግሥቱ ከፍ ብሎአልና እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው ዳዊት አወቀ።
3. ዳዊትም በኢየሩሳሌም ሚስቶችን ጨምሮ ሌሎችን ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች ወለደ።
4. በኢየሩሳሌምም የወለዳቸው የልጆቹ ስም ይህ ነው፤ ሳሙስ፥
5. ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥
6. ኤሊፋላት፥ ኖጋ፥ ናፌቅ፥ ያፍያ፥
7. ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት።
8. ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ ሰሙ፥ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ሊጋጠማቸው ወጣ።
9. ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ አደጋ ጣሉ።
10. ዳዊትም። ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም። በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ አለው።
11. ወደ በአልፐራሲም ወጡ፥ በዚያም ዳዊት መታቸው። ዳዊትም። ውኃ እንዲያፈርስ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በእጄ አፈረሳቸው አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በአልፐራሲም ብለው ጠሩት።
12. አማልክቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፤ ዳዊትም አዘዘ፥ በእሳትም አቃጠሏቸው።
13. ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ በሸለቆው አደጋ ጣሉ።
14. ዳዊትም እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም። ከእነርሱ ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ ወደ እነርሱ አትውጣ።
15. በሾላውም ዛፍ እራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ሊመታ እግዚአብሔር በፊትህ ይወጣልና በዚያን ጊዜ ወደ ሰልፍ ውጣ አለው።
16. ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ከገባዖንም ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መቱት።
17. የዳዊትም ዝና በየአገሩ ሁሉ ወጣ፤ መፈራቱንም እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ አደረገው።

  1Chronicles (14/29)